ኮንፌድሬሽንስ ካፕ፡ ኢትዮጵያ በአዲስ ህንፃ እና ኡመድ ኡኩሪ ትወከላለች 

የ2016 የካፍ ኮንፌድሬሽን ካፕ የሁለተኛ ዙር የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ዛሬ ፣ ቅዳሜ እንዲሁም እሁድ ሲደረጉ የአዲስ ህንፃ ክለብ የሆነው አሃሊ ሸንዲ በሜዳው የጋና ኤፍኤ ዋንጫ አሸናፊው ሚዲአማን ያስተናግዳል፡፡ የኡመድ ኡኩሪ ክለብ የሆነው ኢኤንፒፒአይ ደግሞ ወደ ጋቦን ተጉዞ ሲኤፍ ሞናናን ሊበርቪል ላይ ይገጥማል፡፡

መከላከያ በቅድመ ማጣሪው ዙር በግብፁ ምስር አል ማቃሳ በ6-1 የአጠቃላይ ውጤት ከውድድር ውጪ ከሆነ በኃላ ኢትዮጵያ በኮንፌድሬሽን ካፑ ላይ ተወካይ ክለብ የላትም፡፡ ነገር ግን በሱዳን እና ግብፅ ክለቦች የሚጫወቱት አማካዩ አዲስ ህንፃ እና አጥቂው ኡመድ ኡኩሪ በውድድሩ ላይ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ተጫዋቾች ሆነዋል፡፡

ከወር በፊት ኢኤንፒፒአይ የኮትዲቯሩን አፍሪካ ስፖርትስ ዲ አቢጃን 6-1 በሆነ የአጠቃላይ ውጤት ሲያሸንፍ ግብ ያስቆጠረው ኡመድ ከሞናና ጋር ለሚኖረው ጨዋታ ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ይካተታል የሚል ሰፊ ግምት ተሰጥቷል፡፡ በሱዳን የተሳካ የእግርኳስ ህይወትን እየመራ የሚገኘው አዲስ ህንፃም ክለቡ አል አሃሊ ሸንዲ ሚዲአማን በሚገጥመው ቡድን ውስጥ ተኳቷል፡፡ በቅርቡ በጋና ፕሪምየር ሊግ ድንቅ ብቃቱን እያሳየ የሚገኘው አጥቂው አባስ መሃመድ ለሸንዲ ተከላካዮች ፈተና ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በሰሜን አፍሪካ ደርቢ የሞሮኮው ካውካብ አትሌቲክ ማራካሽ ኤምኦ ኦራንን ይገጥማል፡፡ ሁለቱ ክለቦች በኮንፌድሬሽን ካፕ ላይ የገነነ ስም ባይኖራቸውም ወደ ሶስተኛው የማጣሪያ ዙር ለማለፍ ከፍተኛ ትንቅንቅ ያደርጋሉ፡፡

የዩጋንዳው ቪላ ራባት ላይ ከኤፍዩኤስ ራባት ጋር አርብ ጨዋታውን ያደርጋል፡፡ የዩጋንዳው ፕሬዝደንት ዩሪ ሙሴቪኒ በፋይናንስ ቀውስ ውስጥ ለሚገኘው ለቪላ የ120ሺህ የአሜሪካ ዶላር ለደርሶ መልስ ጨዋታው ውጪ እንዲሆን ሰጥተዋል፡፡ ቪላ የመጀመሪያ ዙር የመልስ ጨዋታውን ከዛንዚባሩ ጄኬዩ ለማድረግ 25 ሰዓታትን የፈጀ የየብስ እና ውሃ ጉዞ ለማድረግ ተገዷል፡፡

የታንዛኒው አዛም ከቱኒዚያው ኤስፔራንስ እንዲሁም የአልጄሪያው ሲኤስ ኮንስታንታይን ከምስር አል ማቃሳ የሚያደርጉት ጨዋታዎች ከአሁን የብዙዎች የአፍሪካ እግርኳስ ተመልካቾችን ቀልብ ስቧል፡፡

 

የሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች

አርብ

20፡30 – ፋዝ ዩኒየን ስፖርት ራባት (ሞሮኮ) ከ ስፖርት ክለብ ቪላ (ዩጋንዳ)(ኮምፕሌክስ ስፖርቲፍሞላይ አል ሃሰን)

ቅዳሜ

15፡00 – ዛናኮ ኤፍሲ (ዛምቢያ) ከ ስታደ ጋቢሲየን (ቱኒዚያ)(ሰንሴት ስታዲየም)

18፡00 – መውሊዲያ ክለብ ደ ኦራን (ቱኒዚያ) ከ ካውካብ አትሌቲክ ክለብ ማራካሽ (ሞሮኮ) (ስታደ አህመድ ዛባና)

18፡00 – ሲኤስ ኮንስታንታይን (አልጄሪያ) ከ ምስር አል ማቃሳ (ግብፅ) (ስታደ መሃመድ ሃምላዊ)

ዕሁድ

15፡00 – ሲኤፍ ሞናና (ጋቦን) ከ ኢኤንፒፒአይ (ግብፅ) (ስታደ አውገስቲን ሞንዳን ደ ሲባንግ)

15፡15 – አዛም (ታንዛኒያ) ከ ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ (ቱኒዚያ) (አዛም ኮምፕሌክስ ስታዲየም)

15፡30 – ቪ ክለብ ማካንዴ (ኮንጎ ብራዛቪል) ከ ሳግራዳ ኤስፔራንስ (አንጎላ) (ስታደ ሙኒሲፓል ደ ፖይንት ኖይር)

20፡00 – አል አሃሊ ሸንዲ (ሱዳን) ከ ሚዲአማ (ጋና) (ሸንዲ ስታዲየም)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *