ቻን | አሠልጣኝ ውበቱ አባተ እና መስዑድ መሐመድ ከነገው ጨዋታ በፊት መግለጫ ሰጥተዋል

👉 \”እዚህ የመጣነው ያለንን ሁሉንም ነገር ለማሳየት ነው\” ውበቱ አባተ

👉 \”በአዘጋጅ ሀገር ምድብ መሆን ትንሽ ከበድ ይላል ፤ ይህ ቢሆንም አሁን ላይ ትኩረታችን ስለነገው የመጀመሪያ ጨዋታ ነው\” መስዑድ መሐመድ

ነገ 10 ሰዓት ኢትዮጵያ እና ሞዛምቢክ የቻን የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ከማድረጋቸው በፊት የዋልያዎቹ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ እና አምበሉ መስዑድ መሐመድ በአልጄሪያ ከሚገኙ የብዙሀን መገናኛ አባላት ጋር የቅድመ-ጨዋታ ቆይታ አድርገዋል። አጠር ባለው ቆይታ በቅድሚያ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ተከታዩን ሀሳብ አጋርተዋል።

\"\"

\”ለዚህ ውድድር ወደ ሞሮኮ በማምራት ዝግጅታችንን የጀመርነው ታኅሣሥ 26 ነው። እዛ በነበረን ቆይታም ከሞሮኮ የቻን ቡድን ጋር ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን አድርገናል። በአጠቃላይ ሞሮኮ ጥሩ ጊዜ አሳልፈናል። አልጄሪያ የደረስነው ከትናንት በስትያ ነበር። ለነገው ጨዋታ በሚገባ ተዘጋጅተናል ፤ በጥሩ ሁኔታ ላይም እንገኛለን።\”

በማስከተል መድረኩን የተረከበው አምበሉ መስዑድ መሐመድ \”ሀገራችን ላይ ጥሩ የልምምድ ጊዜ ነበረን። ከዛም ወደ ሞሮኮ መጥተን የተሻለ ልምምድ አድርገን ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን አድርገናል። በአሁኑ ሰዓት ሁሉም ተጫዋቾች በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ። ምንም የጉዳት ዜና የለብንም። የመጀመሪያ ጨዋታዎችን ለማድረግም ተዘጋጅተናል።\” በማለት ሀሳቡን አጋርቷል።

በውድድሩ ስላላቸው እቅድ እና የቻን ቡድኑ ከዋናው የአፍሪካ ዋንጫ ቡድን ጋር ስላለው መመሳሰል በስፍራው ከተገኙ ጋዜጠኞች የተጠየቁት አሠልጣኝ ውበቱ አባተ \”እዚህ የመጣነው ያለንን ሁሉንም ነገር ለማሳየት ነው። እንደተባለው ይህ ቡድን ከአፍሪካ ዋንጫ ቡድናችን ጋር ተመሳሳይ ነው ፤ 98% የሚሆነው ቡድን ያ ነው። አብዛኞቹ ተጫዋቾቻችን ሀገር ውስጥ የሚጫወቱ ናቸው። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ከሀገር ውጪ የሚጫወቱ ብዙ ተጫዋቾች የሉንም። ነገርግን በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ የሚገቡ አራት ተጫዋቾች በጉዳት ምክንያት ስብስባችን ውስጥ አልተካተቱም። ከዚህ ውጪ ግን ሁሉም ተጫዋቾች ያላቸውን ነገር ለማሳየት ዝግጁ ናቸው። በጨዋታዎቻችንም ጥሩ ጊዜ እንደሚኖረን እናምናለን።\” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።

\"\"

ስለሚገኙበት ምድብ የተጠየቀው መስዑድ መሐመድ በበኩሉ \”በአህጉራችን የሚገኙ ሁሉም ቡድኖች ጠንካሮች ናቸው ፤ ግን በአዘጋጅ ሀገር ምድብ መሆን ትንሽ ከበድ ይላል። ይህ ቢሆንም አሁን ላይ ትኩረታችን ስለነገው የመጀመሪያ ጨዋታ ነው። ምክንያቱም ከባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፏችን የተማርነው ትምህርት አለ ፤ እርሱም በመጀመሪያው ጨዋታ ጥሩ ከሆንክ ለቀጣዮቹ ጨዋታዎች ስንቅ ይሆናል። ይህንን ተከትሎ አሁን ላይ ትኩረታችን የነገው ጨዋታ ነው።\” የሚል ሀሳቡን ገልጿል።