ቻን | የአልጄሪያው አሠልጣኝ መጂድ ቡጌራ ከነገው ጨዋታ በፊት ምን አሉ?

👉 \”ኢትዮጵያዎች ከቀደመው አቀራረባቸው አንፃር ለውጦች እንደሚያደርጉ ብንጠብቅም ምን ሊመስሉ እንደሚችሉ ግን እናውቃለን\”

👉 \”ተጫዋቾቼ ከጨዋታዎች በፊት ባለው ቀን ከማህበራዊ ትስስር ገፆች እንዲርቁ ነግሬያቸዋለሁ\”

👉 \”ካሸነፍን ማለፉችንን እናረጋግጣለን። ሁሉም ጨዋታዎች ለእኛ የፍፃሜ ያህል ናቸው ፤ ስለዚህ ያለንን ሁሉ መስጠት ይኖርብናል\”

ነገ ምሽት 4 ሰዓት ኢትዮጵያ እና አልጄሪያ ከሚያደርጉት የምድብ ሁለተኛ ጨዋታ በፊት የሁለቱ ቡድን አሠልጣኞች እና አምበሎች የቅድመ-ጨዋታ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ከሰዓታት በፊት በዋልያው በኩል የተሰጠውን ሀሳብ ያቀረብን ሲሆን አሁን ደግሞ ምድቡን በበላይነት እየመራች የምትገኘው የአልጄሪያ አሠልጣኝ መጂድ ቡጌራ የሰጡትን ሰፋ ያለ አስተያየት ይዘን ቀርበናል።

\”እያንዳንዱን ጨዋታ እንደ ፍጻሜ እንቀርባለን። የነገው ጨዋታ ለሁለታችንም ቡድኖች አስፈላጊ ነው። ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፋችንን ለማረጋገጥ ድልን አቅደን ወደ ሜዳ እንገባለን። ይህንን ጨዋታ ለማሸነፍ ያለንን ነገር ሁሉ እንሰጣለን።

\”የበለጠ ያላቸውን ብቃት ለማሳየት ነፃ የሆኑ ተጫዋቾችን ለማየት እንሞክራለን። በመጀመሪያው ጨዋታ ጥሩም መጥፎም ነገሮች ነበሩ። መጥፎው ነገር ፍፁም አልነበርንም። በጣም አስፈላጊው ነገር የዐእምሮ ሁኔታ ነው። በዚህ ረገድ የጎደሉን ነገሮች ላይ ሥራዎችን ለመስራት ሞክረናል። በመጀመሪያው ጨዋታ ብዙ ጫናዎች ነበሩብን። በነገው ጨዋታ የመጨረሻ ቅብብላችን የተሻለ የሆነበት እና ጥራት ያለው ማጥቃት የሚሰነዝር ቡድን እናያለን ብዬ አስባለው። ሜዳ ላይ ተጫዋቾች ጥረታቸውን ያለጫና በጋራ እንዲያደርጉ እነግራቸዋለው። ጥሩ ብቃት ያላቸው ተጫዋቾች አሉኝ። በተለይ ታክቲካሊ ዲሲፕሊን በመሆን ረገድ ጥሩ ተጫዋቾች በስብስባችን ይገኛሉ።\” ብለዋል።

\"\"

የቀድሞ የብሔራዊ ቡድኑ አምበል በቀጣይ ስለተጋጣሚው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጠይቀው ይሄንን ብሏል።

\”የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተለዋዋጭ እና ምላሾችን ቶሎ የሚሰጥ ነው። ኳሱን በመጫወቱ ረገድ በጣም ምቾት አላቸው። ኳሱን እንዲጫወቱ ከፈቀድንላቸው የራስ መተማመናቸውን ሊያሳድጉ ይችላሉ። በደንብ ስላጠናናቸው ምን እንደሚጠብቀን እናውቃለን። ይህ ቢሆንም ግን እናከብራቸዋለን። ጨዋታዎችን እያደረክ በሄድክ ቁጥር እየከበዱ እየከበዱ ነው የሚመጡትና ጥሩ የዐምሮ ሁኔታ ላይ መሆን ያስፈልጋል።\”

በማስከተል ከተጫዋች ጉዳት ጋር በተያያዘ አጥቂው አይመን ማሂዎስ እና የአጥቂ አማካዩ ኢስላም ባኪር ስላሉበት ወቅታዊ ሁኔታ \”በሊቢያው ጨዋታ ጉዳት ያስተናገደው ማሂዎስም ሆነ ባኪር ስብስቡን ተቀላቅለው ልምምዳቸውን በጥሩ ሁኔታ እየሰሩ ነው። ዴቢህ ግን ዛሬ ጠዋት የኤም አር አይ ምርመራ ተደርጎለት ውጤቱን እየጠበቅን እንገኛለን።\” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።

ከታክቲካዊ አቀራረብ ጋር በተያያዘ ደግሞ \”እኛ በራሳቸው ሜዳ ተሰብስበው ቢከላከሉም ሆነ ጨዋታውን ከፍተው ቢጫወቱ ለሁለቱም መንገዶች ዝግጁ ነን። ኢትዮጵያዎች ከቀደመው አቀራረባቸው አንፃር ለውጦች እንደሚያደርጉ ብንጠብቅም ምን ሊመስሉ እንደሚችሉ ግን እናውቃለን ፤ ለዚህም ጨዋታውን እንዴት መቅረብ እንዳለብን የራሳችን ሀሳብ አለን።ተጋጣሚያችን ይዞ ለሚመጣው ሁሉም መንገድ ዝግጁዎች ነን ፤ ግን ደግሞ ሁሉም ቡድኖች ጥንቃቄን መርጠው ከእኛ ጋር እንደሚጫወቱ እንጠብቃለን።\” በማለት በልበ ምሉነት ምላሻቸውን በስፍራው ለተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት አጋርተዋል።

በጨዋታው ከተጫዋቾቹ ስለሚጠብቀው የትኩረት ደረጃ ጥያቄ የተጠየቁት መጂድ ቡጌራ በአረብ ዋንጫ ላይ የተፈጠረውን ነገር በማስታወስ ለተጫዋቾች ያስተላለፉትን ትዕዛዝ ተናግረዋል።

\”ተጫዋቾቼ ከጨዋታዎች በፊት ባለው ቀን ከማህበራዊ ትስስር ገፆች እንዲርቁ ነግሬያቸዋለሁ። እዛ ላይ ጊዜ ማጥፋት ኃይልን እንደማባከን ነው። በአርብ ዋንጫ ላይ ከዚህ ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ አጋጣሚዎች ነበሩ ፤ ይህ አደገኛ ልምድ ነው።

\"\"

\”ካሸነፍን ማለፉችንን እናረጋግጣለን። ሁሉም ጨዋታዎች ለእኛ የፍፃሜ ያህል ናቸው ፤ ስለዚህ ያለንን ሁሉ መስጠት ይኖርብናል። መዘናገት አይገባንም። ሁሌም ቢሆን ራሳችንን ለመጨረሻው ፍልሚያ ዝግጁ ማድረግ ይኖርብናል። ለዚህም ሁሌም ራሳችንን መጠየቅ አለብን ብዬ አስባለሁ ፤ ስለሆነም ለነገው ጨዋታ በሙሉ አቅማችን ዝግጁ ሆነን እንቀርባለን ብዬ አስባለሁ።\”

በመጨረሻ የዋናው የአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ጀማል ቤልማዲ የቻን ቡድኑ በትናንትናው ዕለት በብሔራዊ የቴክኒክ ማዕከል (ሲዲ ሙሳ) ልምምዱን ሲሰራ ስለመገኘታቸው ተጠይቀው \”ጀማል በሲዲ ሙሳ ይገኛል ፤ በዚያም የተገኘው እኛን ለመደገፍ ነው። ይህ በጣም ደስ ይላል። ተጫዋቾቼ ልምምድ በሚሰሩበት ወቅት ተመልክተውታል ፤ ይህም ለተጫዋቾቹ ሆነ ለአሰልጣኝ ቡድን አባላት ብርታትን የሚሰጥ ነው። እኔ ከእሱ ጋር በቅርበት ነው የምንሰራው።\” በማለት ከተናገሩ በኋላ የነገውን ጨዋታ አሸንፈው እስከ ውድድሩ ፍፃሜ ለመጓዝ እንደሚያስቡ ተናግረው ጋዜጣዊ መግለጫውን ፈፅመዋል።