ከፍተኛ ሊግ | ደሴ ከተማ ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች አስፈርሟል

በአሰልጣኝ ሲሳይ አብርሀም የሚመራው ደሴ ከተማ የሰባት አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ፈፅሟል።

ከአንድ ዓመት የተሳትፎ መራቅ መልስ ዳግም ወደ ውድድር ተመልሶ በዘንድሮው የከፍተኛ ሊግ ምድብ \’ሐ\’ ስር በአሰልጣኝ ሲሳይ አብርሀም እየተመሩ አንደኛውን ዙር ከመሪው ሀምበሪቾ በአስር ነጥቦች ዝቅ ብሎ በደረጃ ሰንጠረዡ አራተኛ ላይ ተቀምጦ ዙሩን ያገባደደው ደሴ ከተማ በሁለተኛው ዙር ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ለመገኘት ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች ጨምሮ ሰባት አዳዲስ ተጫዋቾችን በሁለተኛው ዙር ውድድር ተጠናክሮ ለመቅረብ በማስፈረም በባቱ ከተማ ዝግጅቱን ቀጥሏል።

\"\"

አዲስ ህንፃ የክለቡ ቀዳማዊ ፈራሚ ሆኗል። የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ፣ ደደቢት ፣ የሱዳኑ አል ሀሊ ሸንዲ ፣ አዳማ ከተማ እና ባሳለፍነው ዓመት በወላይታ ድቻ ካሳለፈ በኋላ በከፍተኛ ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ በከፍተኛ ሊጉ ለመጫወት ወደ ደሴ አምርቷል።

አሌክስ ተሰማ ሌላኛው ፈራማ ሆኗል። በኒያላ ፣ ሀዋሳ ከተማ ፣ መቐለ 70 እንደርታ እና መቻል ተጫውቶ ያሳለፈው የመሀል ተከላካዩ ባሳለፍነው የውድድር ዓመት በመቻል በመጫወት ላይ እያለ በአበረታች መድሀኒት ከመጠቀም ጋር በተያያዘ የአንድ ዓመት ቅጣቱን ፈፅሞ ደሴን ተቀላቅሏል።

ዮናታን ከበደም የቡድኑ አዲስ ፈራሚ ነው። በሀዋሳ ከተማ ፣ ኤሌክትሪክ ፣ ወላይታ ድቻ ፣ አርባምንጭ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ በአጥቂ ስፍራ ላይ ይጫወት የነበረው ተጫዋቹ በካፋ ቡና ያለፉትም ስድስት ወራት ከቆየ በኋላ ነው ወደ ደሴ ያመራው።

ቡድኑ ከሦስት ተጫዋቾች በተጨማሪ የቀድሞው ተጫዋቹ አንስዋር መሐመድን በድጋሚ ከለገጣፎ ለገዳዲ ሲያስፈርም ፣ ዳኛቸው ብርሀኑ ተከላካይ ከሰንዳፋ በኬ ፣ ዳዊት ቀለመወርቅ አማካይ ከለገጣፎ ለገዳዲ ፣ ብሩክ ብርሀኑ የመስመር ከለገጣፎ ለገዳዲ የደሴ አዳዲሶቹ ተጫዋቾች ሆነዋል።

\"\"