በዋልያዎቹ ምድብ የምትገኘው ማላዊ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አድርጋለች

ኢትዮጵያ በምትመራው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ምድብ የምትገኘው ማላዊ በትናንትናው ዕለት የአቋም መለኪያ ጨዋታ አከናውናለች።

\"\"

ከቀናት በኋላ ለሚደረጉት የ2023 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ሦስተኛ እና አራተኛ ጨዋታዎች የአህጉራችን ብሔራዊ ቡድኖች ዝግጅታቸውን እያከናወኑ ይገኛል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባለበት ምድብ የሚገኘው የማላዊ ብሔራዊ ቡድንም ከግብፅ ጋር ላለበት ወሳኝ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ዝግጅቱን ወደ ሳውዲ አረቢያ አምርቶ እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን በትናንትናው ዕለትም ከባንግላዲሽ አቻው ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አከናውኗል።

\"\"

በፕሪንስ መሐመድ ቢን አብዱላዚዝ ስፖርት ሴንተር በተደረገው የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ላይ አሠልጣኝ ማሪዮ ማሪንቻ በ62ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ አሰላለፋቸውን ሙሉ ለሙሉ እንደቀየሩ ከ13 ደቂቃዎች በኋላ በቺዉኪፖ ሙሱዮያ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው መሪ የነበሩ ቢሆንም ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ግብ አስተናግደው ፍልሚያውን አቻ አጠናቀዋል።