ሠራተኞቹ በዛሬው ጨዋታ ዋና አሠልጣኛቸውን አያገኙም

ዛሬ 9 ሰዓት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ጨዋታ ያለባቸው ወልቂጤ ከተማዎች ፍልሚያውን በምክትል አሠልጣኛቸው እየተመሩ እንደሚከውኑት ታውቋል።

በወቅታዊው የደረጃ ሰንጠረዥ 21 ነጥቦችን ሰብስበው 13ኛ ቦታ ላይ የተቀመጡት ወልቂጤ ከተማዎች በባህር ዳር ከተማ ከደረሰባቸው የ17ኛ ሳምንት ሽንፈት በኋላ ዛሬ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ወሳኝ ጨዋታ ይጠብቃቸዋል። በዚህ ጨዋታ ላይ ደግሞ የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ሜዳ ተገኝተው ቡድናቸውን እንደማይመሩ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

\"\"
አሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ከረቡዕ ጀምሮ አዳማ የማይገኙ ሲሆን በቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ፀጋው የማነህ ሀዘን ምክንያት ፍቃድ ጠይቀው ወደ ዲላ እንዳመሩ ታውቋል። በካናዳ የነበረው ወዳጃቸው ፀጋው ህልፈተ ህይወቱ ተሰምቶ አስክሬኑ ወደ ሀገር ቤት ሀሙስ ገብቶ ዓርብ ስርዓተ ቀብሩ ይደረጋል ተብሎ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች በመዘግየቱ አሠልጣኙ በቶሎ ወደ አዳማ መመለስ አልቻሉም። ትናንት ሀገር ቤት በመድረሱ ስርዓተ ቀብሩ በዛሬው ዕለት የሚከናወን ሲሆን አሠልጣኙ የዛሬው ጨዋታ አምልጧቸው ነገ ቡድኑን እንደሚቀላቀሉ ሰምተናል።
\"\"
ዋና አሠልጣኙ አለመኖሩን ተከትሎ ያለፉትን ሁለት ቀናት ልምምድ ያሰራው የቡድኑ ምክትል አሠልጣኝ ዳዊት ሀብታሙ በዛሬው ጨዋታ ስብስቡን ሜዳ ላይ የሚመራ ይሆናል።