መረጃዎች | 73ኛ የጨዋታ ቀን

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በ18ኛው ሳምንት ነገ የሚያስተናግዳቸውን ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎችን አሰናድተናል።

ኢትዮጵያ ቡና ከ ወልቂጤ ከተማ

ሊጉ ነገ በሚያስመለክተን ቀዳሚ ጨዋታ ከ27 ቀናት በኋላ ወደ ሜዳ የሚለሰው ኢትዮጵያ ቡና እና ከሦስት ቀናት በፊት ጨዋታውን ያደረገው ወልቂጤ ከተማ ይገናኛሉ።

ኢትዮጵያ ቡና ከአምስት ተከታታይ አቻዎች በኋላ ለነገው ጨዋታ ይደርሳል። ቡድኑ በመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች መረቡን አያስደፍር እንጂ ከመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች ውስጥ አንድ ጎል ብቻ ማስመዝገቡ ትልቁ ድክመቱ ሆኗል። አሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ በመጨረሻው ጨዋታ ይህንን ሀሳብ አንስተው የነበረ ሲሆን ቡድኑ በልምምድ ላይ ባሳለፋቸው ረጅም ቀናት ከሚፈጥራቸው ጥቂት የማይባሉ ዕድሎች ውስጥ ጎሎችን በማግኘቱ በኩል መሻሻሎች ያሳያል ተብሎ ይጠበቃል። በዚህ ረገድ የመስፍን ታፈሰ ከጉዳት መመለስ ለአሰልጣኙ ሰፊ አማራጭ እንደሚሰጥ ይታመናል። ሆኖም ከተጋጣሚው የጨዋታ ባህሪ አንፃር በአማካይ ክፍል ብልጫ ሊወሰን በሚችለው ጨዋታ አማኑኤል ዮሐንስ በቅጣት አለመኖሩ የቡድኑ ጉድለት ይሆናል። ከዚህ ውጪ ለረጅም ጊዜ በጉዳት ከሜዳ የራቀው አስራት ቱንጆ አሁንም ወደ ሜዳ አይመለስም።

\"\"

ወልቂጤ ከተማ ከነገ ተጋጣሚው አንፃር በቅርብ ቀናት የነጥብ ጨዋታ ማድረጉ በሜዳ ላይ ፍልሚያ መንፈስ ውስጥ ሆኖ ለጨዋታው የመቅረብ ዕድል እንዲኖረው ያደርጋል። ሆኖም በባህር ዳር 4-0 የተረታበትን የዛን ጨዋታ ትዝታ ረስቶ መጀመርም ይጠበቅበታል። በዚህም በእስካሁኑ የዘንድሮው የሊጉ ጉዞው ያስተናገደውን ሰፊ ሽንፈት ተፅዕኖ መቀነስ በአሰልጣኝ ቡድን አባላቱ ዘንድ የቡድኑን የሥነልቦና ደረጃ የማሻሻል ሥራ ይጠበቃል። 12ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሰራተኞቹ እንደሌላው ጊዜ ሁሉ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ይዘው ጥቃቶችን ለመሰንዘር ከመሞከር ባለፈ ተጋጣሚያቸው ላይ ከኳስ ውጪ ከፍ ያለ ጫና በማሳደር ሊጫወቱ እንደሚችሉም ይጠበቃል። ሰራተኞቹ ብዙአየሁ ሰይፈ ፣ አንዋር ዱላ እና ሮበርት ኦዶንካራን በጉዳት ምክንያት ነገ እንደማይጠቀሙ ታውቋል።

ቡድኖቹ እስካሁን ከተገናኙባቸው አምስት ጨዋታዎች አራቱን ኢትዮጵያ ቡና ማሸነፍ ሲችል በአንዱ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ 16 ጎሎች ከመረብ ሲዋሀዱ አስሩ በኢትዮጵያ ቡና ስድስቱ ደግሞ በወልቂጤ ስም የተመዘገቡ ነበሩ።

09:00 ላይ የሚጀምረውን ጨዋታ ተከተል ተሾመ በመሀል ዳኝነት ፣ ዳዊት ገብሬ እና ለዓለም ዋሲሁን በረዳትነት ፣ ሙሉቀን ያረጋል ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል።

ባህር ዳር ከተማ ከ ፋሲል ከነማ

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በሂደት የተለያዩ ቢሆኑም በየፊናቸው ጣፋጭ የሚባሉ ድሎችን ያስመዘገቡት ባህር ዳር እና ፋሲል ተጠባቂ በሆነው ጨዋታ ምሽት 12:00 ላይ ይገናኛሉ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ዛሬ ከሲዳማ ቡና ጋር ነጥብ መጋራቱን ተከትሎ ባህር ዳር ከተማ ከነገው ጨዋታ መሉ ውጤት ካሳካ ከመሪው ጋር ያለውን ልዩነት ወደ ሦስት የመቀነስ ዕድልን ይዞ ወደ ሜዳ ይገባል። ሊጉን ከተቀላቀለበት ጊዜ አንስቶ የተሻለ የሚባል የፉክክር ደረጃ ላይ ለሚገኘው ባህር ዳር ከተማ መሰል በሰንጠረዡ የላይኛው ፍልሚያ ላይ ለውጥ በሚፈጥሩለት ቅፅበቶች ላይ አሸናፊ ሆኖ መውጣት መቻል ከሦስት ነጥብ ባሻገር የተፎካካሪነት ኮስታራነቱ እስከምን ድረስ እንደሆነ የሚመዝንም ጭምር ነው። በመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎቻቸው ሰባት ግቦችን ያስቆጠሩት የጣና ሞገዶቹ ሦስት እና ከሦስት በላይ ጎሎችን ያስቆጠሩ አምስት ተጫዋቾችን መያዛቸውም የጎል ምንጫቸውን ከማብዛት አንፃር በጠንካራ ጎንነት የሚነሳ ነው። ቡድኑ ያለምንም ቅጣት እና ጉዳት ጨዋታውን መጀመር መቻሉም ሌላኛው መልካም ዜና ሆኖለታል።

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን በኃላፊነት ከሾሙ በኋላ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የተሻሻለ ብቃት እያሳዩ የሚገኙት ዐፄዎቹ ተከታታይ ድሎችን ማስነዝገብ የመቻል ጥያቄ ላይ ይገኛሉ። ቡድኑ ከአዳማው ሽንፈት መልስ በወላይታ ድቻው ጨዋታ ከመመራት ተነስቶ ድል ያደረገበት አኳኋን ለቀጣዮቹ ፍልሚያዎች ትልቅ መነሻ መሆን የሚችል ሲሆን የነገው ተጠባቂ ጨዋታ ደግሞ ይህንን እውነታ የሚፈትን ይሆናል። በድቻው ጨዋታ የታየው የኦሴይ ማውሊ የግብ አስቆጣሪነት ብቃት እንዲሁም ቡድንኑ እንደአስፈላጊነቱ በሦስቱም አቅጣጫዎች በተለይም ደግሞ በቀኝ መስመር በድግግሞሽ ያሳየው የማጥቃት ሂደት በነገውም ጨዋታ እንዲደገም የሚሻቸው ነጥቦች ሆነው አልፈዋል። ዐፄዎቹ በነገው ጨዋታ ሱራፌል ዳኛቸውን በቅጣት ፍቃዱ ዓለሙን ደግሞ በጉዳት ምክንያት የማይጠቀሙ ይሆናል።

ሁለቱ ተጋጥሚዎች ከዚህ ቀደም ለሰባት ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን ፋሲል ከነማዎች በሁለቱ ግንኙነቶች በማሸነፍ የበላይነት ያላቸው ሲሆን የተቀሩት አምስት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ነበሩ።

በምሽቱ ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በመሀል ዳኝነት ፣ ኢንተርናሸናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው እና ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት በረዳት ዳኝነት ፣ ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል።

\"\"</a