የትግራይ ክለቦች ወደ ውድድር እንዲመለሱ የድጋፍ ጥሪ ቀርቧል

የትግራይ እግርኳስ ፌዴሬሽን የባለድርሻ አካላት ትብብር ጠይቋል።
\"\"
የትግራይ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በስሩ የሚገኙና በፕሪምየር ሊግ ፣ በከፍተኛ ሊግ ፣ ብሄራዊ ሊግ እና ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የሚሳተፉ ዘጠኝ ክለቦች በቀጣይ ዓመት ወደ ውድድር እንዲመለሱ አስፈላጊው ትብብር እንዲደረግላቸው በይፋዊ ደብዳቤ ጥሪ አቅርቧል።

ፌዴሬሽኑ ይፋ ባደረገው እና የአራት ባለድርሻ አካላት ማለትም የኢትዮጵያ ባህልና ስፖርት ኮሚሽን ፣ የኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽን ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና ኦሎምፒክ ኮሚቴን ትብብር በጠየቀበት ደብዳቤ ክለቦቹ ወደ ውድድር እንዲመለሱ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ድጋፎች እንዲደረግላቸው መጠየቁን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።
\"\"
በተለያዩ ግዜያት ከክልሉ ክለቦች ጋር ውይይት ያደረገው የክልሉ ፌዴሬሽን ከውይይቱ በኋላ የአካባቢው እግር ኳስ እንቅስቃሴ ከቀድሞ አሰራር ለማሻሻል ዘጠኝ አባላት ያሉት ኮሚቴ አቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱ ይታወሳል።