ከፍተኛ ሊግ | የ22ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች

ዛሬ በከፍተኛ ሊጉ ከተደረጉ ጨዋታዎች መካከል ተጠባቂ ከነበሩት ውስጥ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያሸነፈበት እንዲሁም ገላን ከተማ ነጥብ የጣለበት ውጤቶች ተመዝበዋል።

በዳንኤል መስፍን እና ጫላ አቤ

ምድብ ሀ

የዕለቱ የመጀመርያ ጨዋታ በንግድ ባንክ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በትናትናው ዕለት የቤንች ማጂ ቡና ነጥብ መጣሉን ተከትሎ የዛሬውን የንግድ ባንክ እና የሀላባ ከተማን ጨዋታ ተጠባቂ እንዲሆን ያደረገው ሲሆን ገና ከጨዋታው ጅማሮ አንስቶ ጎል ፍለጋ ማጥቃት የጀመሩት ንግድ ባንኮች በ6ኛው ደቂቃ በአቤል ሀብታሙ ጥሩ አጨራረስ አማካኝነት ቀዳሚ የሆኑበትን ጎል ማስቆጠር ችለዋል። በዚህች ጎል የተነቃቁት ንግድ ባንኮች ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠረ ተጭነው መጫወታቸውን ቀጥለው ሁለተኛ ጎላቸውን በ29ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። ለመጀመርያው ጎል መቆጠር ኳሱን አመቻችቶ ያቀበለው ብሩክ ብፁአምላክ በተመሳሳይ በጥሩ መንገድ ያቀበለውን አቤል ሀብታሙ ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛውን ጎል አስገኝቷል። ወደ እረፍት መዳረሻ ላይ የሀላባው የመስመር አጥቂ አቡሽ ደርቤ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት አንበሉ ሠኢድ ግርማ ለቡድኑ ጎል አድርጎታል።

\"\"

በሁለተኛው አጋማሽ ተሽለው የመጡት ሀላባዎች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን እንቅስቃሴዎችን ማደረግ ቢችልሙ የጠራ የጎል ሙከራ ለማድረግ ተቸገሩ እንጂ ንግድ ባንኮችን ጫና ውስጥ ከተዋቸው ነበር። በአሰላ አረንጓዴ ስታዲየም ዝናብ መጣሉን ተከትሎ ሁለቱም ቡድኖች የሚፈልጉትን እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ ዝናቡ አግዷቸዋል። በዝናብ የቀጠለው ጨዋታው በ73ኛው ደቂቃ ንግድ ባንጎች ጨዋታውን መቆጣጠር የቻሉበትን ጎል ተቀይሮ በገባው ወንድማገኝ ኬራ አማካኝነት ሦስተኛ ጎል ማግኘት ችለዋል። በቀሩት ደቂቃዎች ብዙ የተለየ ነገር ሳይኖር ጨዋታው በንግድ ባንክ አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ ንግድ ባንክ ከተከታዮ ቤንች ማጂ ቡና ያለውን ነጥብ ወደ ሦስት ከፍ በማድረግ ምድቡን በቀዳሚነት እየመራ ይገኛል።

ቀጥሎ በተካሄደው የሰበታ ከተማ እና የጋሞ ጨንጫ ጨዋታ ሰበታ አንድ ለምንም አሸናፊ ሆኗል። ምንም እንኳን በሁለቱም በኩል በርከት ያሉ የጎል ዕድሎች አይፈጠሩበት እንጂ ጥሩ ፉክክር ያስመለከተን ጨዋታ ነበር። በ10ኛው ደቂቃም በጨዋታው ብቸኛ ጎል ሊቆጠርም ችሏል።

 ከረጅም ርቀት የተሻገረውን ኳስ የጋሞ ጨንቻው ተካላካይ አማኑኤል ተፈራ ለግብ ጠባቂ ለማቀበል ያሰበው ኳስ በቀጥታ ወደ ጎልነት በመቀየር ሰበታን መሪ አድርጓል። የአሰላው ውድድር መካሄድ ከጀመረ አንስቶ አንድም ጨዋታ ያልተሸነፈው ጋሞ ጨንቻ ውጤቱን ለመቀየር ብርቱ ጥረት ቢያደርግም ሊሳካለት ሳይችል ቀርቷል።በአንፃሩ በአሰላ አጀማመራቸው ጥሩ ያልነበረው ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻሉ የመጡት ሰበታ ከተማዎች ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት ያደረጉት ተጋድሎ ፍሬአማ ሆኖላቸው ጨዋታውን አንድ ለምንም አሸንፈው አጠናቀዋል። ውጤቱን ተከትሎ ሰበታ ከተማዎች ከወራጅ ከጠናው እራሳቸውን ለማውጣት ሦስት ደረጃዎችን በማሻሻል አስረኛ ሲቀመጡ ጋሞ ጨንቻዎች ባሉበት አራተኛ ደረጃ ተቀምጠዋል።

የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ በአዲስ ከተማ ክ/ከ እና በወሎ ኮንቦልቻ መካከል ተካሂዶ ያለ ጎል ተጠናቋል።

ምድብ ሐ

በዚህ ምድብ ከተደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ሁለቱ አቻ ተጠናቀዋል። ረፋድ ላይ የተደረገው የካ ክ/ከተማ እና ኮልፌ ክ/ከተማ ጨዋታ ቀዳሚ ሲሆን የመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ እና ፈጣን የሆነ እንቅስቃሴ አስመልክቷል። ኮልፌ ክ/ከተማ በፊሊሞን ገብረ ፃድቅ የሚመራው የመሀል ክፍል ጥሩ እንቅስቃሴ ያስመለከቱን ሲሆን የካ ክ/ከተማዎች የጨዋታ ብልጫ በመውሰድ ኳስን ተቀባብለው ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውል። አጋማሹም ምንም ግብ ሳይቆጠር ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽም እንደ መጀመሪያው ተመሳሳይ አጨዋወት የተመለከትን ሲሆን ሁለቱም ክለቦች የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። ሆኖም ግብ ሁለቱም ክለቦች ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ጨዋታው ተጠናቆ ሁለቱም ክለቦች ነጥብ ተጋርተው ሊወጡ ችለዋል።

ቀትር 8 ሰዓት በተደረገው ጨዋታ ደግሞ ሮቤ ከተማ በጅማ አባ ጅፋር 2ለ1 ተረቷል። በጨዋታው የመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ እና ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የተደረገ ሲሆን ጨዋታው እንደተጀመረ በ20ኛው ሰከንድ ጅማ አባ ጅፋሮች ያገኙትን የግብ እድል በአሚር አብዱ አማካኝነት በማስቆጠር መሪ መሆን የቻሉ ሲሆን ከግቧ መቆጠር በኋላ ሮቤ ከተማዎች መከላከልን መሰረት በማድረግ በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ ጅማ አባጅፋሮች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ኳስን በመቆጣጠር ጫና ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። በ41ኛው ደቂቃ ሮቤ ከተማዎች ያገኙትን ኳስ ወደ ግብ ሞክረው በረኛው የመለሰውን ኳስ አብዱል አዚዝ ኡመር ወደ ግብ በመቀየር አቻ በመሆን አጋማሹ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል ማምራት ችለዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ክለቦች ግብ አስቆጥረው ጨዋታውን ለማሸነፍ ጥረት ሲያደርጉ ጅማ አባጅፋሮች ያገኙትን ኳስ የመጀመሪያውን ግብ ያስቆጠረው አሚር አብዶ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ሙሉአለም ወደ ግብ በመቀየር ጅማ አባጅፋርን ዳግም መሪ ማድረግ የቻለ ሲሆን ጨዋታውም ሌላ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በጅማ አባጅፋር አሸናፊነት ተጠናቋል።

በተጠባቂው የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ገላን ከተማ ከነጌሌ አርሲ ጋር ነጥብ ተጋርቷል። የመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታ ከፍተኛ የሆነ ትንቅንቅ እና ውጥረት የነበረበት ጨዋታ ሲሆን ነጌሌ አርሲዎች መከላከልን መሰረት አርገው በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ ገላን ከተማ ደግሞ ኳስን ተቆጣጥረው በቅብብል ወደ ግብ በመድረስ ግብ ለማስቆጠር ጫና ሲያሳድሩ ተመልክተናል። በዚህም ሁኔታ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

\"\"

ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ከ10 ደቂቃ በኋላ በደጋፊዎች ግጭት ምክንያት ጨዋታው ለ35 ደቂቃዎች ያክል የተቋረጠ ሲሆን ከ35 ደቂቃዎች በኋላ ወደ ጨዋታው መመለስ ችለዋል። ጨዋታውም እንደመጀመሪያው አጋማሽ የገላን ከተማ የበላይነት እና ግብ ለማስቆጠር ጫና የፈጠረ ሲሆን ነጌሌ አርሲዎች ደግሞ በጥብቅ በመከላከል ግብ እንዳይቆጠርባቸው ሲጥሩ ተመልክተናል። ይህንንም ተከትሎ በ82ተኛው ደቂቃ የነጌሌ አርሲው ተከላካይ የሆነው አሊ ቡኖ የገላን ተጫዋች ላይ ጥፋት በመስራቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። ጨዋታውም በአቻ ውጤት ተጠናቆ ነጥብ ተጋርተው ወተዋል።