ከፍተኛ ሊግ | የ22ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ

በከፍተኛ ሊግ የ22ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ቤንች ማጂ ቡና ነጥብ ሲጥል ሀምበሪቾ ዱራሜ በበኩሉ በሰፊ ጎል ልዩነት በማሸነፍ የምድቡን መሪነት ተረክቧል።

በቴዎድሮስ ታከለ እና ጫላ አቤ


ምድብ ሀ

አሰላ ላይ እየተደረጉ የሚገኙት የምድብ ሀ የከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎች በ21ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ቀጥለዋል። ረፋድ ላይ ቡታጅራ እና ወልዲያ ከተማ ያለ ግብ አቻ ሲለያዩ ባቱ ከተማ በበኩሉ አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማን በአሸብር ውሮ ብቸኛ ጎል አሸንፏል። በዚሁ ምድብ ወደ ሊጉ በሚደረገው ፉክክር ከመሪው ንግድ ባንክ በሁለት ነጥብ ብቻ ዝቅ ብሎ የሚገኘው ቤንች ማጂ ቡና ከዱራሜ ከተማ ጋር ሁለት አቻ ተለያይቷል። የቤንች ማጂ ቡናን ግቦች ኤፍሬም ታምሩ እና ጌታሁን ገላዬ ሲያስቆጥሩ የዱራሜ ከተማን ግቦች ደግሞ ወንዱ ፍሬው እና ካፎ ካስትሮ በስማቸው አስቆጥረዋል። በዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ደግሞ ሰንዳፋ በኬ በመሳይ ሰለሞን እንዲሁም ጅማ አባ ቡና በሮቦት ሰላሎ ግቦች አቻ ተለያይተዋል።


ምድብ ለ

በምድብ ለ የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ካፋ ቡናዎች ጂንካ ከተማዎች አምስት ቢጫ ካርድ ያየን ተጫዋች አሰልፈዋል በማለት የክስ አቤቱታን አቅርበው ተጀምረው። ጨዋታው በጥሩ ተነሳሽነት የጀመሩት ካፋዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በፈጠሯቸው ልዩነቶች ግብ አግኝተዋል። 8ኛው ደቂቃ ላይ የጂንካ የኋላ መስመር ተጫዋቾች የሰሩትን ስህተት ተከትሎ የመስመር አጥቂው ከድር ሲራጅ ግብ አድርጓት ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል። ከሁለት ደቂቃዎች መልስ ከከድር ሲራጅ እግር ስር ምንጯን ያደረገች ኳስ በንክኪ ተከላካዩ በረከት ተስፋዬ ራሱ ላይ አስቆጥሯት ካፋዎች 2ለ0 ሆነዋል። ጎል ካስቆጠሩ በኋላ በተወሰነ መልኩ የጨዋታ መልካቸው የደበዘዘው ካፋዎች በጂንካ ከተማ ብልጫ ተወስዶባቸዋል። ማኑሄ ጌታቸው በሳጥን ውስጥ በእጅ ኳስ መነካቱን ተከትሎ የተሰጠችን የፍፁም ቅጣት ምት አግብቷት ቡድኑን ወደ ጨዋታ መልሷል። ደቂቃዎች እየገፉ ሲመጡ ወደ ተቃራኒ የሜዳ ክፍል ሳይቸገሩ የሚደርሱት ጂንካዎች ከአስር ደቂቃዎች በኋላ በናኩመር በቀለ ተጨማሪ ጎል ወደ አቻነት መጥተዋል።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ በይበልጥ ጥቃት መሰንዘራቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ጂንካዎች በኑራ ሀሰን ጎል ከመመራት ወደ መሪነት ሽግግር አድርገዋል። በቀላሉ ለስህተት ተጋላጭ እየሆኑ የመጡት ካፋ ቡናዎች በአምስት ደቂቃ ልዩነት መልካሙ ፉንዱሬ በፍፁም ቅጣት ምት እና በጨዋታ አከታትሎ ሁለት ጎሎችን ከመረብ አሳርፎ የቡድኑን የጎል መጠን ወደ አምስት አሳድገዋል። የጨዋታው መደበኛ ደቂቃ ሊገባድ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ የካፋ ቡናው ቡድን መሪ እና የጂንካ ከተማ ግብ ጠባቂ አቤል በላይ በቀይ ካርድ ከወጡ በኋላ ካፋ ቡና ሦስተኛ ጎልን በተመስገን አማረ አማካኝነት አክለው ጨዋታ ጂንካን 5ለ3 አሸናፊ አድርጎ ተጠናቋል።

\"\"

ከሰዓት በተደረገው ጨዋታ ደግሞ ነቀምት ከተማ በገዛኸኝ ባልጉዳ ድንቅ ብቃት ታግዞ ሦስት ነጥብን ያገኘበትን ድል ቂርቆስ ላይ አስመዝግቧል። በአሰልጣኝ ዘላለም ፀጋዬ የሚመራው ቂርቆስ ክፍለከተማ ጨዋታው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ሙሉ የጨዋታ ብልጫን ያሳዩ ቢሆንም ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ሲገቡ የሚታይባቸው የስልነት ችግር የኋላ ኋላ ዋጋ ያስከፈላቸው ሆኗል። 13ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልመጅድ ሁሴን ወደ ጎል የመታት ኳስ ግብ ጠባቂው ማቲዮስ ሰለሞን ራሱ ላይ ከመረብ ባሳረፋት ግብ ቂርቆሶች ቀዳሚ ሆነዋል።

ከጎሉ በኋላ ትኩረታቸውን ኳስ ቅብብል ላይ ያደረጉት ቂርቆሶች በመልሶ ማጥቃት ገዛኸኝን ያማከለ አጨዋወትን ተግባራዊ ማድረጋቸው ጎል እንዲያገኙ አስችሏቸዋል። 33ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻማን ኳስ ገዛኸኝ ባልጉዳ በግንባር ገጭቶ ከመረብ ሲያሳርፍ ከዕረፍት መልስ 90+1 ገዛኸኝ ከተከላካይ ጋር ታግሎ የላከለትን ኳስ ተጠቅሞ ዳንኤል ዳዊት ሁለተኛ ጎል አድርጓት ጨዋታው በነቀምት ከተማ 2ለ1 ድል አድራጊነት ተጠናቋል።


የሳምንቱ የማሳረጊያ ጨዋታ 10 ሰዓት ሲል በንብ እና ጉለሌ ክፍለከተማ መካከል ተካሂዶ ብርቱ ፉክክርን አስመልክቶን በመጨረሻም ጎል ሳይመዘገብበት 0ለ0 ተደምድሟል።

ምድብ ሐ

በምድብ ሐ ዳሞት ከተማ ሶዶ ከተማን 4ለ1 አሸንፏል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ክለቦች ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን በ12ኛው ደቂቃ ዳሞት ከተማዎች ግብ ለማስቆጠር ወደ ፊት በሚሄዱበት ሰአት ሶዶ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት በመሄድ በፊት አጥቂያቸው መሳይ ማርቆስ አማካኝነት ግብ በማስቆጠር ሶዶ ከተማን መሪ ማድረግ ሲችል በጨዋታውም ዳሞት ከተማዎች ግብ ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት በ37ኛው ደቂቃ በሱልጣን አብዩ አማካኝነት ግብ በማስቆጠር የመጀመሪያው አጋማሽ በአቻ ውጤት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

\"\"

ሁለተኛው አጋማሽ የዳሞት ከተማ የበላይነት የታየበት አጋማሽ ሲሆን አጋማሹ እንደተጀመረ በ49ኛው ደቂቃ ዳሞት ከተማዎች ያገኙትን የግብ እድል ሙሉቀን ተስፋዬ ወደ ግብነት በመቀየር ዳሞት ከተማን መሪ ማድረግ ሲችል ጨዋታውም ቀጥሎ በዳሞት ከተማ በኩል ተቀይሮ የገባው አማኑኤል ተስፋዬ በ64ኛ ደቂቃ ላይ እና በ80ኛ ደቂቃ ሁለት ተከታታይ ግብ በማስቆጠር ዳሞት ከተማዎች ሶዶ ከተማዎችን በሰፊ ግብ እንዲረቱ ያረጉ ሲሆን ጣፋጭ ሶስት ነጥብም ማሳካት ችለዋል።


በምድቡ ሁለተኛ ጨዋታ ሀምበሪቾ ዱራሜ በሰፊ ጎል ደሴ ከተማ ረቷል። የመጀመሪያው አጋማሽ የሀምበሪቾ ዱራሜ የበላይነት የታየበት ሲሆን ይህንንም ተከትሎ ጨዋታው እንደተጀመረ ሀምበሪቾ ዱራሜዎች ከፍተኛ የሆነ ጫና በማሳደር በ15ኛው ደቂቃ ጉልላት ተሾመ ግብ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ የቻለ ሲሆን ከግቧ መቆጠር በኋላም ሀምበሪቾ ዱራሜዎች ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ የሆነ ጫና አሳድረው ሲቀጥሉ ከቋሚ ተሰላፊዎቻቸው ውስጥ ወደ ስድስት ተጫዋቾች ቀይረው ጨዋታውን የጀመሩት ደሴ ከተማዎች የቀዘቀዘ አጨዋወትን አስመልክተውናል። ይህንንም ተከትሎ በ37ኛው ደቂቃ ላይ ሀምበሪቾ ዱራሜዎች በበረከት ወንድሙ አማካኝነት ድንቅ ግብ በማስቆጠር መሪነታቸውን አጠናክረዋል።

ሁለተኛው አጋማሽም ደሴ ከተማዎች እንደመጀመሪያው አጋማሽ ድክመታቸውን ሳያርሙ የገቡ ሲሆን ሀምበሪቾ ዱራሜዎች በ46ኛው ደቂቃ በረከት ወንድሙ ለክለቡ ሶስተኛውን ለራሱ ሁለተኛውን ግብ ከመረብ ሲያዋህድ ጨዋታውም በዚህ ሁኔታ ቀጥሎ በረከት ወንድሙ በ76ኛ ደቂቃ ላይ ለራሱ ሶስተኛ ግቡን ለክለቡ ደግሞ አራተኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል። ብዙም ሳይቆይ በ82ኛው ደቂቃ ዳግም በቀለ የሀምበሪቾ ዱራሜን አምስተኛ ግብ አስቆጥሮ ሀምበሪቾ ዱራሜ ደሴ ከተማን በሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፎ ሙሉ ሶስት ነጥብ ማሳካት ችሏል።