ሪፖርት | ፋሲል ከነማ እና አርባምንጭ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

በዝናባማ አየር ታጅቦ አዝናኝ እንቅስቃሴ ያስመለከተን የፋሲል ከነማ እና የአርባምንጭ ከተማ ጨዋታ በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

በተከታታይ ጨዋታዎች ድል በማድረግ የደረጃ ለውጥ ያደረጉት ፋሲል ከነማዎች ሀድያ ሆሳዕናን ከረታው ስብስባቸው አምሳሉ ጥላሁን ፣ አስቻለው ታመነ ፣ ዱላ ሙላቱ እና በዛብህ መለዮን በሽመክት ጉግሳ ፣ ሱራፌል ዳኛቸው ፣ ሀብታሙ ገዛኸኝ እና ዓለብርሀን ይግዛው ተክተው ወደ ሜዳ ሲገቡ በአንፃሩ ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ በየጨዋታው የሚጠቀሙባቸውን ተጨዋቾች እየቀያየሩ የሚገቡት አርባምንጮች ከባህር ዳር ከተማ ጋር ነጥብ ሲጋሩ ከነበሩት ተጫዋቾች መካከል መኮንን መርዶኪዮስ ፣ አህመድ ሁሴን እና መሪሁን መስቀሌ በይስሀቅ ተገኝ፣ አቡበከር ሻሚል እና ሱራፌል ዳንኤል በመያዝ ለጨዋታው ቀርበዋል።

\"\"

በጨዋታው ውጤት ይዞ ለመውጣት ጥሩ የማጥቃት ምልልሶቹን በሁለቱም በኩል መመልከት የጀመርነው ገና በመጀመርያዎቹ ደቂቃ ነበር። ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ሳጥን ውስጥ በነፃ አቋቋም የሚገኘው ሀብታሙ ገዛኸኝ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ አግኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረው እንዲሁም ከደቂቃዎች በኋላ አቡበከር ሻሚል ከደር ኩሊባሊ ጀርባ የተጣለለትን ኳስ ኤሪክ ካፒያቶ ወደ ጎል የመታውን በተከላካዮች ተደርቦ የወጣው በሁለቱም በኩል ጥሩ አጀማመር ለመጀመር መልካም አጋጣሚ ነበር። በዘጠኝ ደቂቃዎች ውስጥ እነዚህን ለጎል የቀረቡ ሙከራዎችን ከተመለከትን በኋላ በ10ኛው ደቂቃ ሀብታሙ ገዛኸኝ ከመስመር ኳሱን እየገፋ በመሄድ ከርቀት መሬት ለመሬት መቶት ይስሀቅ ተገኝ ወደ ውጭ ያወጣበት የጨዋታው ግልፅ የመጀመርያ የጎል ሙከራ ሆኖ አልፏል።

በፍጥነት ጎሎች እንደሚስተናገድ አይቀሬ እንደሆነ ማሳያ ይመስል የነበረው የመጀመርያው አስር ደቂቃ እንቅስቃሴ በሂደት እየተቀዛቀዘ በሁለቱም በኩል እርጋታ በጎደለው መጣደፍ ኳሶቻቸው እየተቆራረጡ በሚፈልጉት መጠን ተጨማሪ የጎል እድሎችን ለመፍጠር ተቸግረው ጨዋታው ወደ 25 ደቂቃ መዝለቅ ችሏል። ሆኖም በ26ኛው ደቂቃ አቡበከር ሻሚል በጥሩ እይታ ያሻገረውን ተመስገን ደረሰ ኳሱን በተገቢው መንገድ ተቆጣጥሮ ከሳጥን ውጭ በግራ እግሩ አክርሮ የመታው ለጥቂት በገቡ አናት የወጣው እና በ33ኛው ደቂቃ ከሽመክት ጉግሳ የተሻገረውን ሀብታሙ ገዛኸኝ በግንባሩ በመግጨት ወደ ጎል መታው ሲባል ለማቀበል በማሰብ ያመከነው የጨዋታውን እንቅስቃሴ ህይወት የዘራበት ነበር።

በተሻለ በፋሲል ከነማ ላይ ብልጫ ወስደው መጫወት የቻሉት አርባምንጭ ከተማዎች የፋሲል ከነማ ተከላካዮች ከራሳቸው የሜዳ ክልል ማራቅ ያልቻሉትን ኳስ ተመስገን ደረሰ አግኝቶ የመታውን ሳማኪ እንደምንም ተቆጣጥሮት ቢያድንባቸውም አዞዎቹ በስተመጨረሻም የመጀመርያ ጎላቸውን በ41ኛው ደቂቃ አግኝተዋል።

ከአቡበከር ሻሚል ወደ ግራ ሳጥኑ ጠርዝ የላከው ኳስ ኤሪክ ካፒያቶ ተቀብሎ በጥሩ ሁኔታ ያሻገረውን ተመስገን ደረሰ በድንቅ አጨራረስ በግንባሩ በመግጨት ወደ ጎልነት ቀይሮታል። ወደ ዕረፍት መዳረሻ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ሀብታሙ ገዛኸኝ ለጎሉ በቅርብ ርቀት ኳሱን አግኝቶ ያልተጠቀመው ለፋሲል ከነማዎች አቻ የሚያደርጋቸው የሚያስቆጭ ዕድል ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ በቀጠለው ጨዋታ በፍጥነት ወደ እንቅስቃሴ ለመግባት በብዙ ቁጥር በዝተው ተጭነው መጫወት የጀመሩት ፋሲል ከነማዎች 56ኛው ደቂቃ ላይ በዕለቱ የጎል ዕድሎችን እያመከነ ያረፈደው ሀብታሙ ገዛኸኝ ሌላ አጋጣሚ አግኝቶ ይስሀቅ ተገኝ ያዳነበት ቡድኑን የሚያነቃቃ ነበር።

\"\"

በአርባምንጭ በኩል በጥንቃቄ በመከላከል አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት አደጋ ለመፍጠር ይሞክሩ እንጂ በአመዛኙ ከራሳቸው ሜዳ ሳይወጡ አፈግፍገው ለመጫወት ያሰቡ በመሆኑ የመጀመርያ አጋማሽ ከነበራቸው እንቅስቃሴ ወርደው ታይተዋል።

በዚህ ሂደት እንቅስቃሴው ቀጥሎ 68ኛው ደቂቃ ሱራፌል ዳኛቸው ከረጅም ርቀት አክርሮ የመታውን ይስሀቅ ተገኝ እንደምንም ወደ ውጭ አውጥቶበታል። ከዚህ ሙከራ በኋላ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በአዲስ ጉልበት ለማጥቃት በማሰብ የሦስት ተጫዋቾችን ቅያሪ በማድረግ የአቻነት ጎል ፍለጋ ጥረት ማድረጋቸውን ቀጥለው የአርባምንጭ ግብጠባቂ ይስሀቅ ተገኝ ስህተት ዐፄዎቹ ወደ ጨዋታው የገቡበትን ጎል አግኝተዋል። በ78ኛው ደቂቃ ሱራፌል ዳኛቸው ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ይስሀቅ ተገኝ በቀላሉ ኳሱን መቆጣጠር አቅቶት የተፋውን ተቀይሮ የገባው በዛብህ መለዮ አስቆጥሮታል። በቀሩት ጥቂት ደቂቃዎች ብዙም የተለየ ነገር ሳያስመለከተን ጨዋታው አንድ ለአንድ ተጠናቋል።

በተከታታይ ጨዋታ ጠንካራ ቡድን እየገጠማቸው እንደሆነነ የተናገሩት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በቡድናቸው ውስጥ ለውጥ እንዳለ አንስተው ሁሌም በድክመቶቻቸው ላይ እየሰሩ ለቀጣይ ጨዋታ አርመው እንደሚመጡ እና ለማሸነፍ የሚያስችላቸውን መንገድ እንደሚከተሉ ተናግረዋል። ለመሸናነፍ የተደረገው ትግል ጥሩ እንደነበረ የገለፁት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ወደ ጎል እንደሚደርሱት ያህል የመጨረስ ችግር እንዳለ በማከል ይህም የሆነው የጅብ ችኩል በሚለው አባባል ከጉጉት የመጣ መሆኑን በመናገር አሁንም ቡድኑን ለመለወጥ ጠንክረው እንደሚሰሩ አሳውቀዋል።