ከፍተኛ ሊግ | የ24ኛ ሳምንት የዛሬ ውሎ

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ ጨዋታዎች በዝናብ ምክንያት ሲዘዋወሩ በምድብ ሐ ተጠባቂ ጨዋታ ሆምበርቾ ዱራሜ ወሳኝ ድል አሳክቷል።

በጫላ አቤ

ምድብ ሀ

አሰላ አረንጓዴው ስታድየም ላይ በሚከናወነው በዚህ ምድብ ውድድር ቡታጅራ ከተማ በአንተነህ ናደው ብቸኛ ጎል ጅማ አባ ቡናን የረታበት ውጤት ተመዝግቧል። ሆኖም አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከ ከ ሰበታ ከተማ ፣ የሰንዳፋ በኬ ከ ወሎ ኮንቦልቻ እንዲሁም ዱራሜ ከተማ ከ ባቱ ከተማ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ ተላልፏል። ነገ ሜዳው ለጨዋታ አመቺ ከሆነ የዛሬውን ሦስት ጨዋታዎች አሸጋሽጎ ለማጫወት መታሰቡም ታውቋል።

\"\"

ምድብ ለ

ሀዋሳ ላይ በምድብ ለጨዋታዎች ይርጋጨፌ ቡና ሰሜን ሸዋ ደብረብርሀንን 2-1 እንዲሁም ቂርቆስ ክ/ከተማ ካፋ ቡናን በ2-0 ውጤት ሲያሸንፉ ጉለሌ ክ/ከተማ እና ጂንካ ከተማ ያለግብ ተለያይተዋል።

ምድብ ሐ

ዳሞት ከተማ 1-1 ደሴ ከተማ

የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ ጥሩ እና ፈጣን እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን ጨዋታው በተጀመረ በ10ኛው ሰከንድ ዳሞት ከተማዎች ያገኙትን ኳስ በፈጣን ቅብብል ወደ ግብ በመድረስ በሀብታሙ መስፍን አማካኝነት ግብ አስቆጥረው መምራት ችለዋል። ከግቡ መቆጠር በኋላ በተስሏች ሳይመን እና በአዲስ ህንፃ ሚመራው ደሴ ከተማ ኳስን ተቆጣጥረው ግብ ለማስቆጠር ጫና ሲፈጥሩ ተስተውሏል። ዳሞት ከተማዎች ያገኙትን የግብ ብልጫ ለማስጠበቅ ወደ ኋላ በማፈግፈግ ግብ ላለማስተናገድ ጥረት ሲያደርግ ተመልክተናል። የመጀመሪያው አጋማሽ መደበኛ ደቂቃ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃ ደሴ ከተማዎች ያገኙትን ኳስ ዮናታን ከበደ ወደ ግብ በመቀየር ደሴ ከተማን አቻ አድርጎ ወደ መልበሻ ክፍል እንዲያመሩ ማድረግ ችሏል።

\"\"

ሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ የሆነ የኳስ ፍሰትን የተመለከትን ሲሆን ሁለቱም በአልሸነፍም ባይነት ስሜት ተሞልተው ግብ ለማስቆጠር እና ግብ ላለማስተናገድ ከፍተኛ የሆነ ፉክክር ተመልክተናል። በ85ኛው ደቂቃ ላይ በተፈጠረው የተጫዋቾች አለመግባባት የደሴ ከተማ የመሀል ክፍል ተጫዋች የሆነው ሚካኤል ለማ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። ይህንንም ተከትሎ ደሴ ከተማዎች ቀሪ ደቂቃዎችን በጎዶሎ ተጫዋች በመጫወት ግብ ሳያስተናግድ ጨዋታውን በአቻ ውጤት ማጠናቀቅ ችሏል። ሁለቱም ቡድኖች ውጤቱን ተከትሎ ነጥብ ተጋርተው ወተዋል።

የካ ክ/ከተማ 1-1 ነገሌ አርሲ

የካ ክ/ከተማዎች ጥሩ እንቅስቃሴ ባሳዩበት አጋማሽ ድንቅ የሆነ የኳስ ቁጥጥር እና የኳስ ቅብብል አስመልክተውናል ። ይህንንም ተከትሎ በ17ኛው ደቂቃ የካ ክ/ከተማዎች ያገኙትን ኳስ ንጋቱ ጌዴቦ የተሻገረለትን በጭንቅላት በማስቆጠር የካ ክ/ከተማን መሪ ሲያደርግ ከግቧ መቆጠር በኋላ ነጌሌ አርሲዎች በመነቃቃት ወደ ጨዋታው ተመልሰው ብልጫ በመውሰድ ጫና ሲፈጥሩ ተስተውሏል።

\"\"

ሁለተኛው አጋማሽ ሙሉ በሙሉ የነጌሌ አርሲ የበላይነት የታየበትና የመጀመሪያ አጋማሽ ስህተታቸውን አርመው የገቡበት ሆኗል። አጋማሹ እንደተጀመረ በ48ኛው ደቂቃ ነጌሌ አርሲዎች ጫና ፈጥረው ያገኙትን የግብ አጋጣሚ ምስጋናው መላኩ ወደ ግብነት በመቀየር አቻ ማድረግ ሲችል ጨዋታውም በዚሁ ሁኔታ ቀጥሎ ሌላ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር በአቻ ውጤት ተጠናቆ ነጥብ ተጋርተው ሊወጡ ችለዋል።

ሀምበሪቾ ዱራሜ 1-0 ገላን ከተማ

በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ የተጀመረው ይህ ተጠባቂ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ በጣም እልህ የበዛበት እና ትንቅንቅ የታየበት ጨዋታ ሲሆን በሀምበሪቾ ዱራሜ በኩል የኋላ ደጀን የሆነው እንዳለ ዮሐንስ እንዲሁም በመሀል ክፍሉ አቤል ዘውዱ እና በፊት መስመሩ በበረከት ወንድሙ የሚመራው ሀምበሪቾ ዱራሜ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ አድርጎ ተጋጣሚው ላይ ብልጫ መውሰድ ችሏል። በገላን ከተማ በኩል በነስረዲን ኃይሌ የሚመራው የኋላ ክፍል እንዲሁም የፊት መስመሩ የኋላሸት ፍቃዱ እና በየነ ባንጃው የማጥቃቱን ሂደት በጥሩ ሁኔታ ሲያከናውኑ ተስተውሏል።

\"\"

በጨዋታው በሁለቱም በኩል የማጥቃት ሂደትን የተመለከትን ሲሆን በ19ኛው ደቂቃ ሀምበሪቾ ዱራሜዎች በመልሶ ማጥቃት የተገኘውን ኳስ በረከት ወንድሙ በማስቆጠር መሪ መሆን የቻሉ ሲሆን ከግቧ መቆጠር በኋላ ገላን ከተማዎች ወደ ፊት ተስበው ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ በአንፃሩ ሀምበሪቾ ዱራሜዎች ወደ ኋላ በመሳብ የሚያገኙትን ኳስ በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ ተስተውሏል።

ሁለተኛው አጋማሽ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሀምበሪቾ ዱራሜ ጥንቃቄን መሠረት ያደረገ አጨዋወት መርጦ ግብ ላለማስተናገድ እና የያዘውን የግብ የበላይነት ለማስጠበቅ ሲጫወት ገላን ከተማዎች ባላቸው አቅም ወደፊት በመሄድ ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ ተስተውሏል። ጨዋታውም በዚሁ ቀጥሎ በ88ኛ ደቂቃ ላይ የሀምበሪቾ ዱራሜ ተጫዋች የሆነው ቶሎሳ ንጉሴ በፈፀመው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። ጨዋታውም ሌላ ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ በሀምበሪቾ ዱራሜ ድል አድራጊነት ተጠናቆ ቡስኑ ጣፋጭ ሦስት ነጥብ በማሳካት ምድቡን በሦስት ነጥብ ልዩነት መምራት ችሏል።

\"\"