መረጃዎች | 93ኛ የጨዋታ ቀን

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 23ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን የሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።

ባህር ዳር ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

ቀን 9 ሰዓት ላይ 44 ነጥቦችን በመያዝ 2ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት የጣና ሞገዶቹ ለዋንጫ የሚያደርጉትን ትንቅንቅ  አጠናክሮ ለመቀጠል በ 31 ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጡት እና በጥሩ መሻሻል ላይ ከሚገኙት ቡናማዎቹ ጋር የሚያደርጉት ፉክክር ይጠበቃል።

ተከታታይ አምስት ጨዋታዎችን ድል አድርገው የነበሩት የጣና ሞገዶቹ ባለፉት ሁለት የጨዋታ ሳምንታት ግን ከኢትዮጵያ መድን እና አርባምንጭ ከተማ ጋር በተመሳሳይ 2-2 ውጤት ነጥብ ሲጋሩ በውድድሩ ካስቆጠሯቸው 39 ግቦች 19 (48.71%) የሚሆኑት ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች ብቻ መቆጠራቸው የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደር የለሽ መሆኑን ቢጠቁምም ካስተናገዷቸው 19 ግቦች 8(42.1%) የሚሆኑት በእነዚህ ጨዋታዎች ላይ መቆጠራቸው አሁንም ከኳስ ጋር ጠንካራ የሆነውን የተከላካይ መስመር ከኳስ ውጪ ያለውን አንጻራዊ ደካማነት በቶሎ ማረም እንደሚገባው ይጠቁማል። በነገው ዕለትም ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያላቸውን የሰባት ነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ተመሳሳይ የጨዋታ መንገድ ከሚከተሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ጋር ብርቱ ፍልሚያ ይጠብቃቸዋል ተብሎ ይገመታል።

\"\"

በመጨረሻ የጨዋታ ሣምንታት በተለይም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ወደ ሚፈልጉት እንቅስቃሴ እየመጡ ያሉ የሚመስሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ይህንን ጠንካራ እንቅስቃሴ ግን ቁጥራዊ መረጃዎች ካስቆጠሩት ግብ ውጪ አይደግፍላቸውም። ካለፉት 10 ጨዋታዎች በሁለቱ ብቻ አሸንፈው በስምንቱ አቻ የተለያዩት ቡናማዎቹ በርካታ ስኬታማ ቅብብሎችን በሚፈልገው የጨዋታ መንገዳቸው ውጤታማ ለመሆን ጊዜ የሚያስፈልጋቸው ይመስላል። ሆኖም የአጥቂ መስመራቸው በመጨረሻዎቹ የድሬዳዋ እና የአዳማ ጨዋታዎች ስድስት ግቦችን ማስቆጠሩ ተስፋ እንዲሰንቁ የሚያደርጋቸው ነው። ሆኖም ግብ በማስቆጠር እና አመቻችቶ በማቀበል በግሩም ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኘው መሐመድኑር ናስር በነገው ጨዋታም ልዩነት ፈጣሪ ተጫዋች ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

ባሕርዳር ከተማ አለልኝ አዘነን ከቅጣት መልስ ማግኘቱ እና ሙሉ ስብስቡ ለጨዋታው ዝግጁ መሆኑ ሲጠቆም በኢትዮጵያ ቡና በኩል ለረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ ከሚገኘው አስራት ቱንጆ በቀር እንደ ተጋጣሚው ቡድን ሁሉ ቀሪው ስብስብ ለጨዋታው ዝግጁ መሆኑ ተሰምቷል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ 7 ጊዜያት ተገናኝተው ባህር ዳር ከተማ ሁለት ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ አንድ ጊዜ ድል ሲያደርጉ አራቱ ጨዋታዎች አቻ የተጠናቀቁ ናቸው። በግንኙነታቸውም ባህርዳር ከተማ 10 ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 12 ግቦችን አስቆጥረዋል።

ጨዋታውን ቢንያም ወርቅአገኘሁ በመሐል ዳኝነት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት እና ካሳሁን ፍፁም በረዳትነት ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ድሬዳዋ ከተማ

በ 11 ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡትን ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በ 27 ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጡት ድሬዳዋ ከተማዎች የሚያገናኘው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ማሳካት ከሚፈልጉት ዕቅድ አንጻር እጅግ አስፈላጊያቸው የሆነውን ድል ለማግኘት ምሽት 12 ሰዓት ላይ ጥሩ ፉክክር ያደርጉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ያሳኩ እንጂ ከእንቅስቃሴ አንጻር መሻሻሎችን በማሳየት ሦስት ግቦችን ማስቆጠር የቻሉት ኤሌክትሪኮች አሁንም ቢሆን የራሳቸው የግብ ክልል ውስጥ የሚሠሯቸው ስህተቶች ድል እንዳያደርጉ ማነቆ ሆነውባቸዋል። 13ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው አርባምንጭ ከተማ በ 13 ነጥቦች ዝቅ ብሎ ለሚገኘው ቡድኑ በሊጉ ለመቆየት ድል ከማድረግ ውጪ ሌላ ውጤት ተቀባይነት አይኖረውም። ሆኖም ለዚህ ዕቅድ ይረዳው ዘንድ በነገው ዕለት ሦስት ነጥብ ለማሳካት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ጠንካራ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅበታል።

\"\"

በውድድር ዓመቱ ከለገጣፎ ለገዳዲ (51) በመቀጠል ሁለተኛውን ከፍተኛ የግብ መጠን (36) ያስተናገዱት ብርቱካናማዎቹ በአዲሱ አሰልጣኛቸው ሥር መነቃቃት የታየባቸው ቢመስልም በድጋሚ ወደ ውጤት ማጣት ቀውስ እያጋደሉ ይመስላል። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ስድስት ግቦች በማስተናገድ ሽንፈት የገጠመው ቡድኑ በተለይም በመስመር ተከላካዮች የሚፈጥረውን የግብ ዕድል በመቀነስ ብልጫ ለመውሰድ አልሞ ከሚገባው መሃል ሜዳው ላይ በሚነሱ ኳሶች የግብ ዕድል ለመፍጠር ፍላጎት እያሳየ ሲሆን ቡድኑ የአጥቂዎቹ በአንድ ለአንድ ግንኙነት ወቅት ደካማ መሆን እና አማካዮቹ በተጋጣሚ ቡድን ተሸፍነው ከጨዋታ ውጪ ሲደረጉ ተቀያሪ ዕቅድ በመተግበሩ በኩል የታየበትን ክፍተት በጊዜ ማረም ይገባዋል።

በኤሌክትሪክ በኩል ፀጋ ደርቤ በጉዳት ጨዋታው የሚያልፈው ሲሆን በድሬዳዋ ከተማ በኩል ያሲን ጀማል እና ያሬድ ታደሰ በጉዳት የማይኖሩ ተጫዋቾች ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ15 ጊዜያት ተገናኝተው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ለ ስድስት ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ ለ ሦስት ጊዜያት ሲያሸንፉ ቀሪዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ የተጠናቀቁ ነበሩ። ኤሌክትሪክ 20 ድሬዳዋ ደግሞ 12 ግቦችን ማስቆጠርም ችለዋል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ ዋና ዳኝ ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው እና እሱባለው መብራቱ ረዳቶች እንዲሁም ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው አራተኛ ዳኛ ሆነው ለዚህ ጨዋታ ተመድበዋል።