መረጃዎች | 96ኛ የጨዋታ ቀን

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 24ኛ ሣምንት የመጀመሪያ ቀን የሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

በሳምንቱ ቀዳሚ መርሐግብር 31 ነጥቦችን በመያዝ 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡትን ኢትዮጵያ ቡናዎች በ 11 ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጡት ኤሌክትሪኮች ሲያገናኝ ሁለቱም ማሳካት ከሚፈልጉት ግብ አንጻር ጥሩ ፉክክር ያደርጉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ባህርዳር ከተማ ላይ ቀድመው ግብ ቢያስቆጥሩም የኋላ የኋላ 3 ግቦችን አስተናግደው 3ለ1 የተረቱት ቡናማዎቹ ያሳዩት ደካማ እንቅስቃሴ ከጨዋታ ሳምንቱ በፊት በነበሩት ሁለት ጨዋታዎች ያሳዩትን የጨዋታ ግለት ያቀዘቀዘ ነበር። አሁንም ቢሆን ካላቸው ስብስብ አንጻር ወደ ውጤት ለመመለስ ብዙም የሚቸገሩ ባይመስሉም ጠንካራ ጎናቸው የነበረው  የተከላካይ መስመራቸው ባለፉት 3 ጨዋታዎች 6 ግቦችን ማስተናገዱ አሁንም ቢሆን በጥልቅ መፈተሽ እንዳለበት የሚጠቁም ነው። ሆኖም በእነዚህ ጨዋታዎች 7 ግቦችን ያስቆጠረው የማጥቃት ኃይላቸው አሁንም ለቡድኑ ድል መቀዳጀት ሲባል በተደራጀ መልኩ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

\"\"

ከለገጣፎ ለገዳዲ (54) በመቀጠል ሁለተኛውን ከፍተኛ የግብ መጠን (37) ያስተናገዱት ኤሌክትሪኮች በእንቅስቃሴ ደረጃ እያሻሻሉ ቢመጡም ቁጥሮች ግን ይህንን አይደግፉም። ካለፉት አራት የጨዋታ ሣምንታት አንድ ነጥብ ብቻ ያሳካው ቡድኑ በእነዚህ ጨዋታዎች ሁሉ ተመሳሳይ ሁለት ሁለት ግቦችን ሲያስናግድ ሦስት ግቦችን ተጋጣሚው ላይ ማሳረፍ ችሏል። በውድድር ዓመቱ ከለገጣፎ (14) እና ሀዲያ ሆሳዕና (19) በመቀጠል ከወላይታ ድቻ ዕኩል ሦስተኛውን ዝቅተኛ የግብ መጠን (20) ያስቆጠሩት ኤሌክትሪኮች ከኳስ ጋር ጠንካራ ለሆነው ቡድኑ ይህ ደካማ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለናፈቃቸው ድል  እንደ አንድ ምክንያት ይቆጠራል። በተለይም ባለፈው የጨዋታ ሣምንት በድሬዳዋ ከተማ 2-0 ሲሸነፉ በፈጠሯቸው የግብ ዕድሎች ውስጥ የግቡ አግዳሚ የመለሰባቸው እና ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ ካመከናቸው አንዱ እንኳን መረብ ላይ ቢያርፍ የጨዋታውን ውጤት ሊቀይር የሚችል አጋጣሚ ነበር። ሆኖም ከወራጅ ቀጠናው ውጪ ካለው ሲዳማ ቡና በ 16 ነጥቦች ዝቅ ብሎ የሚገኘው ቡድኑ በሊጉ ለመትረፍ ያለውን የመነመነ ተስፋ ለማጠናከር ድልን ብቻ አስቦ በነገው ዕለት ከኢትዮጵያ ቡና ጠንካራ ፍልሚያ ይጠብቀዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ ቡና አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ ሲመለስለት ከአሥራት ቱንጆ በተጨማሪ አማኑኤል አድማሱን በጉዳት ያጣል። በኤሌክትሪክ በኩል ደግሞ ማታይ ሉል በአምስት ቢጫ የነገው ጨዋታ የሚያመልጠው ይሆናል።

አዳማ ከተማ ከ ባህር ዳር ከተማ

የምሽቱ መርሐግብር 32 ነጥቦችን በመያዝ 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡትን አዳማ ከተማዎች በ 47 ነጥቦች 2ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጡት ባህርዳር ከተማዎች ሲያገናኝ አዳማዎች ካለፉት ሁለት የአቻ ውጤቶች በኋላ ወደ ድል ለመመለስ የጣና ሞገዶቹ ደግሞ ወደ ዋንጫ የሚያደርጉትን ግስጋሴ ለመቀጠል ብርቱ ፉክክር ያደርጉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

በመቀመጫ ከተማቸው ካደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች ሦስቱን በመርታት በአንዱ አቻ ተለያይተው በሁለቱ የተሸነፉት አዳማዎች ባለፈው የጨዋታ ሣምንት በሀዋሳ ከተማ ቆይታቸው ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ከወላይታ ድቻ ጋር ነጥብ ተጋርተዋል። በሊጉ አምስተኛውን ከፍተኛ የግብ መጠን (32) ከተጋጣሚያቸው መረብ ላይ ያሳረፉት አዳማዎች በወጣቶች ላይ ባላቸው ፅኑ እምነት ውጤታማ መሆናቸውን ቀጥለዋል። አሰልጣኝ ይታገሡ እንዳለ የሚመርጡት በርካታ ስኬታማ ቅብብሎችን አድርጎ ትዕግሥትን በሚፈልግ የማጥቃት ሂደት የግብ ዕድሎችን የሚፈጥረው ቡድን ቀስ በቀስ እየተዋሃደ ሄዶ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ቢቀመጥም በቡድኖች መካከል ያለው የነጥብ መቀራረብ አሁንም ቢሆን ተደላድሎ ለመቀመጥ ድል እንደሚያስፈልጋቸው ይጠቁማል።

\"\"

ባለፉት ስምንት ጨዋታዎች ሁሉ ሁለት እና ከዛ በላይ ግብ ማስቆጠር የቻሉት የጣና ሞገዶቹ ከአምስት ተከታታይ ድሎች በኋላ ሁለት አቻ ተለያይተው አራት ነጥቦችን ቢጥሉም ይፈተኑበታል ተብሎ በተገመተው የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ግን ከመመራት ተነስተው ድል ተቀዳጅተዋል። በየትኛውም የሜዳ ክፍል እንከን የማይወጣለት ቡድኑ በየ ጨዋታው የሚፈጥራቸው የግብ ዕድሎች ላይ ግን ምህረት የለሽ መሆን ይጠበቅበታል። የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመቻል መሸነፉን ተከትሎ የነጥብ ልዩነቱን ወደ አራት ያጠበቡት ባህርዳሮች ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ርስ በእርስ በሚገናኙበት ጨዋታ የራሳቸውን ዕድል ለመወሰን ከዚያ በፈት ያሉትን ጨዋታዎች ግን በትኩረት ማድረግ ይገባቸዋል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ ሰባት ጊዜያት ተገናኝተው ባህር ዳር ከተማ አምስቱን በመርታት የበላይነቱን ሲወስድ አንዱ ጨዋታ በአቻ አንዱ ደግሞ በአዳማ አሸናፊነት ተጠናቋል። በግንኙነታቸው ባህርዳር ስምንት አዳማ ደግሞ አንድ ግብ ማስቆጠር ችለዋል።