ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና በሮቤል ተ/ሚካኤል ብቸኛ የፍጹም ቅጣት ምት ግብ ኤሌክትሪክን ረቷል

በ24ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ያልቻሉት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በኢትዮጵያ ቡና 1-0 መረታታቸው በውድድር ዓመቱ ያስተናገዱትን ሽንፈት 15 አድርሶታል።

\"\"

ቀን 9 ሰዓት ላይ የሳምንቱ የመጀመሪያ መርሐግብር በኢትዮጵያ ቡና እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ መካከል ሲደረግ ቡናዎች በ 23ኛው ሣምንት በባህር ዳር ከተማ 3-1 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የአምስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ግብ ጠባቂው ሕዝቄል ሞራኬ ፣ ገዛኸኝ ደሳለኝ ፣ ኩዋኩ ዱሃ ፣ ብሩክ በየነ እና አንተነህ ተፈራ ወጥተው ግብ ጠባቂው በረከት አማረ ፣ ወልደአማኑኤል ጌቱ ፣ ኃ/ሚካኤል አደፍርስ ፣ አብዱልከሪም ወርቁ እና ጫላ ተሺታ ገብተዋል። ኤሌክትሪኮች በአንጻሩ በተመሳሳይ የጨዋታ ሳምንት በድሬዳዋ ከተማ 2-0 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ያሬድ የማነ ፣ ፀጋ ደርቤ እና ፍፁም ገ/ማርያም በ ማታይ ሉል ፣ አብዱልራህማን ሙባረክ እና ኢብራሂም ከድር ተተክተው ጀምረዋል።


ቀዝቀዝ ብሎ በጀመረው የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር ሲደረግበት የጠሩ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን ኢትዮጵያ ቡናዎች ቀስ በቀስ ብልጫውን መውሰድ ችለዋል። 19ኛው ደቂቃ ላይ ወልደአማኑኤል ጌቱ ከራሱ የግብ ክልል በረጅሙ ያሻማውን ኳስ በጥሩ ጊዜ አጠባበቅ ያገኘው መሐመድኑር ናስር ከግብ ጠባቂው ከፍ አድርጎ (ቺፕ) የሞከረውና ዒላማውን ሳይጠብቅ የወጣው ኳስ የአጋማሹ የተሻለው የመጀመሪያ ለግብ የቀረበ ሙከራ ነበር።


በጥሩ ቅብብሎች በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ቡናማዎቹ ጨዋታው 36ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ በሴኮንዶች ልዩነት በሁለት አጋጣሚዎች ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። በቅድሚያም በቀኙ የማጥቂያ መስመራቸው ራምኬል ጀምስ ከራሱ የግብ ክልል በረጅም ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ጫላ ተሽታ ለአማኑኤል ዮሐንስ አቃብሎት አማኑኤልም በግሩም ዐይታ መሐመድኑር ናስርን ከግብ ጠባቂ ጋር ያገናኘ ኳስ ማመቻቸት ቢችልም መሐመድኑር ናስር በወረደ አጨራረስ የግብ ዕድሉን አባክኖታል። በሴኮንዶች ልዩነትም ከግራው የሳጥኑ ከፍል ላይ የነበረው ኃ/ሚካኤል አደፍርስ ያሻገረውን ኳስ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ ሆኖ ያገኘው ጫላ ተሺታ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተሻሽሎ ሲቀጥል 52ኛው ደቂቃ ላይ ቡናዎች ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ተቀይሮ የገባው አንተነህ ተፈራ ሳጥን ውስጥ በግንባሩ የገጨውን ኳስ ተስፋዬ በቀለ በእጁ በመንካቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ሮቤል ተክለሚካኤል መረቡ ላይ አሳርፎታል። ከአራት ደቂቃዎች በኋላም ሮቤል ተክለሚካኤል ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው መሐመድኑር ናስር በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቷል።


ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በመጠኑ የተሻሻሉት ኤሌክትሪኮች 77ኛው ደቂቃ ላይ አብነት ደምሴ ከሳጥን ውጪ ካደረገው ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ውጪ የተሻለ የግብ ዕድል ለመፍጠር ተቸግረው በሙሉ ደቂቃ አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ቡናዎችም ጨዋታውን መምራት ከጀመሩ በኋላ ጨዋታውን አቀዝቅዘው ሲቀጥሉ 78ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ በየነ ከቅጣት ምት ሞክሮት ግብ ጠባቂው ጋክፖ ሸረፍዲን በቀላሉ ከያዘው ኳስ ውጪ የኤሌክትሪክን የተከላካይ መስመር መፈተን ተስኗቸዋል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ቡና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

\"\"

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የኢትዮ ኤሌክትሩኩ አሰልጣኝ ስምዖን ዓባይ \”ከቦርድ ጀምሮ ደጋፊዎች በሜዳ እየተገኙ እየደገፉ ነው ፤ የቀረው ከኛ ነው።\” ብለው ንግግራቸውን ሲጀምሩ እንደ መሐመድኑር ናስር ያሉ የቡናን ተጠባቂ ተጫዋቾች ለማጥፋት አስበው እንደገቡ እና ይህም እንደተሳካላቸው ሲገልጹ የነበራቸውን የኳስ ቁጥጥር ወደ ውጤት አለመቀየራቸው ዋጋ እንዳስከፈላቸው እና ቡና ባልጠበቁት አሰላለፍ ወደ ሜዳ እንደገባ ሲጠቁሙ \”ከሊጉ ብንወርድ እንኳን የተሻለ እንቅስቃሴ እና ውጤት ይዘን ለመውረድ ነው የምናስበው።\” በማለት አበክረው ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ በበኩላቸው ቡድናቸው ከባለፈው ሳምንት የተሻለ አቀራረብ ቢኖረውም የሚቀረው ነገር እንዳለ ሲጠቁሙ። ጫላ ተሺታ ከነ ጉዳቱ መግባቱ ተጨምሮበት እንደጠበቁት ባለማግኘታቸው ዕረፍት ላይ እሱንም ሆነ አላለለፋቸውን እንደቀየሩ እና ካለባቸው ጫና ለመውጣት እየታገሉ እንደሆነ ሲናገሩ በተጫዋቾች የመጨረስ አቅም ላይ ጥያቄ እንዳላቸው ነገር ግን ይፈታል ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋል።