ሪፖርት | የጣና ሞገዶቹ ወሳኝ ድል አዳማ ከተማ ላይ አሳክተዋል

ተቀይሮ የገባው አደም አባስ ቡድኑ ባህር ዳር ከተማ ከአዳማ ከተማ ሦስት ነጥብ ወስዶ ከመሪው ጋር ያለው ልዩነት ወደ አንድ እንዲያጠብ አድርጓል።

\"\"

በ23ኛ ሳምንት ከወላይታ ድቻ ጋር ነጥብ የተጋራው አዳማ ከተማ ሁለት ነጥብ ከጣለበት ቋሚ አሰላለፍ ሁለት ተጫዋቾችን ለውጧል። በዚህም አዲስ ተስፋዬ እና አሜ መሐመድ አርፈው አቡበከር ወንድሙ እና ቦና ዓሊ ጨዋታውን ጀምረዋል። በተመሳሳይ የጨዋታ ሳምንት ኢትዮጵያ ቡናን 3ለ1 የረታው ባህር ዳር ከተማ በበኩሉ አንድም ተጫዋች ሳይለውጥ ወደ ሜዳ ገብቷል።


በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ለመዝለቅ የወጠኑት ባህር ዳር ከተማዎች ጨዋታው እንደተጀመረ ወዲያው ፈጣን ጥቃት ሰንዝረው መሪ ሊሆኑ ነበር። በዚህም ከቀኝ መስመር የተነሳውን ኳስ ሀብታሙ ታደሠ ከተከላካዮች አፈትልኮ በመውጣት ያገኘውን ኳስ ለፉአድ ፈረጃ አቀብሎ የአጥቂ አማካዩ የመታውን ኳስ ተከላካዩ እዮብ ማቲያስ በጥሩ ሸርተቴ መልሶታል። ከመጀመሪያው ሙከራ በኋላ የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ወደ ራሳቸው ያመጡት አዳማ ከተማዎች ደግሞ በ9ኛው ደቂቃ ቦና ዓሊ ከርቀት በመታው ኳስ የጨዋታውን የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርገው ተመልሰዋል።

ፈጣኖቹን አጥቂዎች ለመጠቀም የሚሞክሩት አዳማዎች ገና በጨዋታው መባቻ በጉዳት ምክንያት አማኑኤል ጎበናን ተክቶ የገባው ቢኒያም ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ በተሰጠ የቅጣት ምት ዮሴፍ ታረቀኝ ግብ ለማስቆጠር ቢጥርም የግቡ አግዳሚ ከግብነት ታድጎታል። ይሁ ተጫዋች የቅጣት ምቱን ከሞከረ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ሌላ የሰላ ሙከራ ሰንዝሮ ነበር። ወደ ጎል በመሄድ ረገድ ብልጫ የወሰዱት አዳማዎች በ25ኛው ደቂቃም ከወትሮ ቦታው በተለየ በቀኝ መስመር ተከላካይነት በተሰለፈው አቡበከር ወንድሙ አማካኝነት ጥቃት ሰንዝረው ተመልሰዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊገባደድ የዳኛው ፊሽካ በሚጠበቅበት ቅፅበት ደግሞ ፍፁም ጥላሁን ከተከላካይ ጀርባ በመሮጥ የደረሰውን ኳስ መረብ ላይ አሳረፈ ተብሎ ሲጠበቅ በወረደ አጨራረስ አምክኖት ቡድኖቹ ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።


አካላዊ ጉሽሚያዎች በርከት ባሉበት ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በድፍረት ወደ መሐል ሜዳው ጠጋ ብለው ሲጫወቱ የነበረ ሲሆን በዚህ ሂደት ከተከላካይ ጀርባ የሚገኙ ቦታዎችን ለማጥቃት ፈጣን ሽግግሮች ሲከወኑ አስተውለናል። የአጋማሹ የመጀመሪያ የሰላ ሙከራም በ59ኛው ደቂቃ በአዳማ ከተማ በኩል ተደርጓል። በዚህም ቦና ዓሊ ከወደቀኝ ካደላ መስመር ከርቀት አክርሮ መትቶ የግብ ዘቡ ፋሲል ገብረሚካኤል ተቆጣጥሮበታል።

በማጥቃቱ ረገድ ውጤታማ መሆን ያልቻሉት ባህር ዳር ከተማዎች የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ለውጠው ክፍተታቸውን ለማረም ጥረት አድርገዋል። ይህ ለውጣቸው በመጠኑ እድገት ቢያመጣም ኩዋሜ ባህን የፈተነ ሙከራ ማድረግ ግን አልቻሉም። በተቃራኒው አዳማ ከተማዎች በ74ኛው ደቂቃ ፈቱዲን ጀማል የተሳሳተውን ኳስ ተጠቅመው ሳይታሰብ ቀዳሚ ሊሆኑ የነበረ ቢሆንም የግብ ዘቡ የአጋሩን ስህተት አርሟል።


ጨዋታው 79ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግብ ተቆጥሯል። በተጠቀሰው ደቂቃም ዱሬሳ ሹቢሳ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ፍፁምን ተክቶ ለገባው አደም አባስ አመቻችቶለት ፈጣኑ አጥቂ በቀኝ እግሩ ኳስ እና መረብን አገናኝቶ ቡድኑን መሪ አድርጓል። ከግቡ በኋላ አዳማዎች ቢያንስ የአቻ ውጤት ለማግኘት ቢጣጣሩም ባህር ዳሮች እጃቸው የገባውን ሦስት ነጥብ አስጠብቀው ወጥተዋል። በተለይ በጭማሪው ደቂቃ አቡበከር ያሻማውን ኳስ ነቢል ኑሪ በግንባሩ የሞከረው ኳስ ለአቻነት እጅግ የቀረበች ነበረች።

\"\"

ከጨዋታው በኋላ ድል ያደረጉት አሠልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ጨዋታው እግጅ ፈታኝ እንደነበረ በመጠቆም ተጫዋቾቻቸው በፈታኙ ጨዋታ ላገኙት ድል አድናቆት ሰጥተዋል። ከዋንጫ ፉክክሩ ጋር ተያይዞ ደግሞ ትኩረታቸው ከፊታቸው ላለው ጨዋታ እንደሆነ ተናግረዋል። የአዳማ ከተማው አሠልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በበኩላቸው በጨዋታው ከዚህ በፊት ከነበራቸው ነገር ወጥተው ሲጫወቱ እንደነበርና ችኮላዎች እንደነበሩ ገልፀው አንድ ነጥብ ቢጠብቁም ውጤቱን እንደሚቀበሉ ተናግረዋል።