ከፍተኛ ሊግ | ሀምበሪቾ ዱራሜ ነጥብ ቢጋራም የገላን አቻ መውጣት ወደ ፕሪምየር ሊጉ የማደጉን ዕድል አስፍቶለታል

በተጠባቂው የምድብ ሐ ጨዋታ ሀምበሪቾ እና ገላን ከተጋጣሚያቸው ጋር ነጥብ ተጋርተው ሀምበሪቾ የማደጉን ዕድል ሲያሰፋ በምድብ ሀ ደግሞ ሰንዳፋ በኬ እና ቡታጅራ ወደ አንደኛ ሊግ መውረዳቸውን ተረጋግጧል።

በዳንኤል መስፍን እና ጫላ አቤ

ምድብ ሀ

ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ ብርቱ ፉክክር የተደረገበት ጨዋታ በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከ አሸናፊነት ተገባዷል።

ከ14ኛው እስከ 23ኛው ሳምንት ድረስ በአሰላ አረንጓዴ ስታዲየም ሲካሄድ የቆየው የከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ ውድድር በከተማ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ አበበ አበበ ቢቂላ ስታዲየም እንዲቀየር በማድረግ ውድድሩ በዛሬ ዕለት በይፋ በአቃቂ ቃሊቲ እና በሰበታ ከተማ መካከል ተጀምሯል።

\"\"

በእንቅስቃሴ ኳሱን ተቆጣጥሮ በመጫወት ሰበታ ከተማዎች አጀማመራቸው ጥሩ የሚባል ቢሆንም ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ የነበሩት አቃቂዎች ነበሩ። በ11ኛው ደቂቃ በጥሩ መንገድ የተሻገረለትን ኳስ እሸቱ ጌታሁን ቡድኑን ቀዳሚ አድርጎበታል። ብዙም ሳይቆይ የመጀመርያውን ጎል ያስቆጠረው አጥቂው እሸቱ ጌታሁን ያቀበለውን ማሩፍ መሐመድ በጥሩ አጨራረስ ሁለተኛ ጎል ለአቃቂዎች አስገኝቷል። ተከታታይ ሁለት ጎል ቢያስተናግዱም ወደ ጨዋታው ለመግባት ጥረት ያደረጉት ሰበታዎች በ23ኛው ደቂቃ በኤፍሬም ቀሬ የግል ጥረት ጎል አስቆጥረው ለመነቃቃት ሞክረዋል።


በሁለተኛው አጋማሽ በጥብቅ እየተከላከሉ የጥንቃቄ አጨዋወት የመረጡት አቃቂዎች ጨዋታውን መቆጣጠር የቻሉበትን ጎል አግኝተዋል። ጎሉንም በዕለቱ ኮከብ በነበረው እሸቱ ጌታውን አማካኝነት ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል አስገኝቶ ጨዋታው ተጠናቋል። አቃቂዎች ማሸነፋቸውን ተከትሎ ለከርሞ በሊጉ ለመቆየት ያላቸውን ተስፋ ሲያለመልሙ በአንፃሩ ሰበታ ከተማዎች ከፕሪሚየር ሊጉ ወርደው ከፍተኛ ሊጉን በተቀላቀሉበት ዓመት ዳግመኛ ወደ አንደኛ ሊግ ላለመውረድ ቀጣይ ጨዋታዎቻቸው ማሸነፍ እንዲሁም የሌሎች ቡድኖችን ውጤት የመጠበቅ ግዴታ ውስጥ እንዲገቡ አስገድዷቸዋል። የአቃቂን ማሸነፍ ተከትሎ ቡታጅራ ግን ወደ አንደኛ ሊግ መውረዱ ተረጋግጧል።

በመቀጠል የተካሄደውን ጨዋታ ወሎ ኮምቦልቻን ባለ ድል አድርጓል።


በመውረድ ስጋት ውስጥ ሆነው ሁለቱም ቡድኖች ጨዋታቸውን እንደማድረጋቸው መጠን ያደረጉትን እንቅስቃሴ ሳቢ አልነበረም። በአንፃራዊነት ወሎዎች ወደ ጎል በመድረስ የተሻሉ የነበረ ቢሆንም ኳስና መረብን ለማገናኘት አልቻሉም። ሰንዳፋ በኬዎች ሽንፈት ከሊጉ እንደሚያወርዳቸው በማሰብ በራሳቸው የሜዳ ክፍል በቁጥር በዝተው አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር የጠራ የጎል ዕድል ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጫና የፈጠሩት ወሎ ኮንቦልቻዎች ተቀይሮ በገባው ዮናታን ኃይሉ በ71ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ብቸኛ ጎል አሸንፈው ሊወጡ ችለዋል። በውጤቱም ሰንዳፋ በኬዎች ወደ አንደኛ ሊግ መውረዳቸውን ሲያረጋግጡ። ወሎ ኮምቦልቻ በሊጉ ለመቆየት በቀጣይ ሳምንት ከአቃቂ ቃሊቲ ጋር የሚያደርጉት ወሳኝ ጨዋታ ማሸነፍ ለሁሉም ነገር መልስ የሚሰጥ ይሆናል።

የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ የነበረው እና በአማረ የጋሞ ጨንቻ ደጋፊዎች ድባብ ታጅቦ የተካሄደው የጋሞ ጨንቻ እና የሀላባ ከተማ ጨዋታ ጥሩ ፉክክር አስመልክቶን ያለ ጎል ተጠናቋል።


ምድብ ለ

የነጌሌ አርሲ እና ዳሞት ከተማ ከተማ የረፋድ ጨዋታ በነጌሌ አርሲ አንድ ለምንም አሸናፊነት ተቋጭቷል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ እና አዝናኝ ጨዋታ የተመለከትን ሲሆን በዳሞት ከተማ በኩል አዲስ ወርቁ በተከላካይ ስፍራ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ሲያደርግ ተስተውሏል። በነጌሌ አርሲ በኩል ብሩክ ቦጋለ እና በሰለሞን ገመቹ የሚመራው የመሀል ክፍል ድንቅ እንቅስቃሴዎችን አስመልክተውናል። በአጋማሹም ምንም ግብ ሳይቆጠር በአቻ ውጤት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።


በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ዳሞት ከተማዎች የተጫዋች ቅያሬ በማድረግ የተወሰደባቸውን የኳስ ብልጫ ለመውሰድ ጥረት ቢያደርጉም ነጌሌ አርሲዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ መልኩ ግብ ለማስቆጠር ጫና ሲያደርጉ ተስተውሏል። ይህንንም ተከትሎ በ 71ኛው ደቂቃ ነጌሌ አርሲዎች ያገኙትን ኳስ ብሩክ ቦጋለ በማስቆጠር መሪ ያደረጋቸው ሲሆን ጨዋታውም በዚው ውጤት ተጠናቆ ነጌሌ አርሲ ድል ማድረግ ችሏል።

ከሰዓት 9 ሰዓት በሼር እና ባቱ ሜዳ የተደረጉት ተጠባቂዎቹ ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተፈፅመዋል።

አንድ ለአንድ የተጠናቀቀው የገላን ከተማ እና የካ ክ/ከተማ የመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታ ጥሩ ፉክክር እና ትንቅንቅ የታየበት ሲሆን ገላን ከተማ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ መልካም የሆነ አጨዋወት አስመልክተውናል። የካ ክ/ከተማዎች ኳስን በመከላከል የሚያገኙትን ኳስ በመልሶ ማጥቃት ወደ ተቃራኒ ቡድን ለመድረስ ሲጥሩ ተመልክተናል። ገላን ከተማዎች በ29ኛው ደቂቃ ያገኙትን የግብ እድል በሲሳይ ጥበቡ አማካኝነት በማስቆጠር ገላን ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል። የካ ክ/ከተማዎች ከግቧ መቆጠር በኋላ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። ይህንንም ተከትሎ በ 34 ደቂቃ ያገኙትን ኳስ አንዱአለም ሾሌ ወደ ግብ ቀይረው አቻ በመሆን ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።


ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ ቀዝቀዝ ያለ አጨዋወት የተመለከትን ሲሆን በአጋማሹም ምንም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ቡድኖቹ በአቻ ውጤት ነጥብ ተጋርተው መውጣት ችለዋል።

የሀምበሪቾ ዱራሜ እና ስልጤ ወራቤ ጨዋታ ያለ ግብ ቢጠናቀቅም ሀምበሪቾ የገላን ነጥብ መጋራትን ተከትሎ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የማለፉን ዕድል አስፍቷል። የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታ ጥሩ እንቅስቃሴ ያስመለከተ ሲሆን የመጀመሪያው አጋማሽ የሀምበሪቾ ዱራሜ የበላይነት የታየበት እና ቶሎ ቶሎ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያስመለክተን ቆይቷል። ስልጤ ወራቤዎች መከላከል ላይ ትኩረት በማድረግ በመልሶ ማጥቃት የሚያገኙትን ኳስ ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል። አጋማሹም ያለምንም ግብ ተጠናቆ በአቻ ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።


ከዕረፍት መልስ ሀምበሪቾ ዱራሜ አጨዋወታቸውን በመቀየር በረጃጅም ኳስ እና በመስመር በማጥቃት ጥሩ ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን ሲሞክሩ በአንፃሩ ስልጤ ወራቤ ጥሩ ጥሩ የግብ እድሎችን መፍጠር ቢችሉም ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ጨዋታው ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቆ ነጥብ ሊጋሩ ችለዋል። ሀምበሪቾም በቀጣይ ሳምንት አንድ ነጥብ ብቻ ካሳካ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የሚያልፍበትን ሁነት የሚፈጥር ይሆናል።

\"\"