መረጃዎች | 97ኛ የጨዋታ ቀን

የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎችን በተመለከተ የቅድመ መረጃዎችን እንደሚመለከተው አሰናድተናል።

አርባምንጭ ከተማ ከወላይታ ድቻ

በ7 ነጥቦች እና በ3 ደረጃዎች ተበላልጠው የተቀመጡት እንዲሁም ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በተመሳሳይ የአንድ አቻ ውጤት ያስመዘገቡት አርባምንጭ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ነገ እርስ በእርስ የሚያደርጉት ጨዋታ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት እና የሊጉን የወገብ በላይ ደረጃ ለማግኘት ጥሩ ፉክክር ይደረግበታል።

ካለፉት ዘጠኝ ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ያሸነፈው አርባምንጭ ከተማ ራሱን አስጊ ቦታ ላይ ያገኘ ይመስላል። እርግጥ ቡድኑ በእንቅስቃሴ ረገድ ባለፉት ጨዋታዎች ለመጥፎ የሚዳርግ ብቃት ባያሳይም በተለይ የኋላ መስመሩ ክፍተት ዋጋ እንዲከፍል እያደረገው ነው። በሚገርም ሁኔታም ከነገ ተጋጣሚው ወላይታ ድቻ እንዲሁም ከአዳማ ከተማ ጋር ካደረጋቸው የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች ውጪ ግቡን ሳያስደፍር ወጥቶ የማያውቀው ቡድኑም ከደረጃ ሰንጠረዡ ቅርቃር ለመውጣት የግድ ግቦችን በቀላሉ መፍቀድ የለበትም። የፊት መስመሩ ጥሩ በመሆኑም የኋላ መስመሩ ከተስተካከለ ከአስጊው ቀጠና ሊወጣ እንደሚችል ይታሰባል።

\"\"

ስምንት ተከታታይ ጨዋታዎችን ድል ሳያደርጉ ከተጓዙ በኋላ ሁለት ድል ከመቻል እና ለገጣፎ የወሰዱት ወላይታ ድቻዎች ባሳለፍነው ሳምንት ከአዳማ ከተማ ጋር ነጥብ ቢጋሩም ጥሩ አቋም ላይ ያሉ ይመስላል። አዳማ ላይ በተደረጉት ጨዋታዎች የአጨዋወት ለውጥ በማድረግ ጨዋታዎችን ሲቀርብ የነበረው ቡድኑ አሁን የሚታወቅበትን ቀለም ብዙም ሳይለቅ በአዲሱ ከኳስ ጋር የማሳለፍ ባህሪ እየተንቀሳቀሰ ተጋጣሚን እያስገረመ ይገኛል። ይህ \’ደፈር\’ የማለት ባህሪ ነገም እንደሚታይ የሚገመት ሲሆን ከላይ እንደገለፅነው አርባምንጭ በመከላከሉ ረገድ ችግሮች ስላሉበት ይህንን ክፍተት ለመጠቀም እንደሚሞክሩም ቀድሞ ይገመታል።

ከዚህ ቀደም ሁለቱ ቡድኖች 13 ጊዜ የተገናኙት ሲሆን ስምንቱ ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት ሲፈፅሙ ወላይታ ድቻዎች አራት እንዲሁም አርባምንጭ ከተማዎች ደግሞ አንድ ጊዜ ማሸነፍ ችለዋል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከወልቂጤ ከተማ

በመካከላቸው አራት ነጥብ ቢኖርም በደረጃ ረገድ ስድስተኛ እና አስራ ሁለተኛ ቦታ ላይ የተቀመጡት ሀዲያ ሆሳዕና እና ወልቂጤ ከተማ በምሽቱ የነገ ጨዋታ የሚያሳዩት እንቅስቃሴ ሳቢ እንደሚሆን ይጠበቃል።

በአሠልጣኝ ያሬድ ገመቹ የሚመራው ሀዲያ ሆሳዕና እንደ ሊጉ ክስተት ቡድን እየታየ ሲሆን ያለፉትን ሦስት ጨዋታዎች ግን አንድም ድል አላሳካም። በተለይ በአጥቂ መስመሩ ላይ የወጥነት ችግር ያለበት ስብስቡ በድብልቅ አጨዋወት ለተጋጣሚ ቀላል የማይባል ፈተና የሚቸር ቢሆንም የጨዋታ ላይ ኃያልነቱን በግብ የሚያሳጅብለት አስተማማኝ አጥቂ አለማግኘቱ ከዚህም በላይ የተሻለ ደረጃ ላይ እንዳይገኝ አድርጎታል። ለዚህም ማሳያ ተጋጣሚ ላይ ግብ በማስቆጠር በሊጉ ደረጃ ቢወጣ ሀዲያ 15ኛ ቦታ ላይ ይቀመጥ ነበር። በተቃራኒው ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመቀጠል ሁለተኛው ትንሽ ግብ ያስተናገደ መሆኑ በቀላሉ እጅ እንዳይሰጥ ረድቶታል።

ከሜዳ ውጪ ባሉ ችግሮች እየታመሰ የሚገኘው ወልቂጤ ከተማ ሜዳ ላይ ግን ችግሮች ያሉበት አይመስልም። በተለይ ባሳለፍነው ሳምንት በለገጣፎ ለገዳዲ 2ለ0 እየተመራ በ45 ደቆቃዎች ውስጥ አስገራሚ ቅልበሳ በማሳየት ያሳካው ጣፋጭ ድል የተጫዋቾቹን ብርታት በሚገባ የሚያሳይ ነው። ይህ ጨዋታም ለነገው እና ለቀጣይ ጨዋታዎች በተለይ ከወራጅ ስጋት ለመራቅ በሚያደርገው ትግል ትልቅ ስንቅ እንደሚሆነው ይታሰባል። እርግጥ የነገ ተጋጣሚው ሀዲያ ከላይ እንዳነሳነው ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ባለቤት ስለሆነ እንደ ለገጣፎ ጨዋታ ቀላል ፈተና ላይገጥመው ስለሚችል ጠንክሮ መጫወት የግድ ይለዋል።

\"\"

ሀድያ ሆሳዕና ቃልአብ ውብሸት እና ቤዛ መድህን ከጉዳታቸው ያላገገሙለት ሲሆን ባዬ ገዛኸኝም ቅጣት ላይ በመሆኑ በጨዋታው አይሳተፍለትም። ወልቂጤ ከተማ በነገው ጨዋታ የአምስት ተጫዋቾችን ግልጋሎት አያገኝም። ተከላካዩ ውሀብ አዳምስ በቅጣት ምክንያት ከጨዋታው ውጪ ሲሆን አንዋር ዱላ፣ ተመስገን በጅሮንድ፣ አፈወርቅ ኃይሉ እና አቡበከር ሳኒ ደግሞ በጉዳት ፍልሚያው የሚያመልጣቸው ይሆናል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም አምስት ጊዜ ተገናኝተው አራቱ ጨዋታዎች በነጥብ መጋራት ሲጠናቀቁ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ደግሞ የተቀረችውን አንድ ጨዋታ ማሸነፍ ችለዋል።