የዋልያዎቹ ተጋጣሚ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ልታደርግ ነው

ሰኔ 13 ከኢትዮጵያ ጋር የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ያለባት ማላዊ ለጨዋታው የምታደርገውን ቅድመ ዝግጅት ስትቀጥል በቀጣዩ ሳምንትም የአቋም መለኪያ ጨዋታ ለመከወን ቀጠሮ ይዛለች።

በአይቮሪኮስት አዘጋጅነት ለሚከናወነው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎች እየተከናወኑ ሲሆን ሀገራችን ኢትዮጵያም ከግብፅ፣ ማላዊ እና ጊኒ ጋር ተደልድላ ጨዋታዎችን እያደረገች ትገኛለች። ከቀናት በኋላም ከማላዊ ጋር የምድብ 5ኛ ጨዋታዋን በገለልተኛ ስታዲየም ሞዛምቢክ ላይ ታከናውናለች።
\"\"
የኢትዮጵያ ተጋጣሚ የሆነችው ማላዊ ከቀናት በፊት እንዳስነብነው ለጨዋታው ከፍ ያለ ትኩረት በመስጠት በሀገር ውስጥ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን በሳምንት ሦስት ቀን እያሰባሰበች ያለፉትን ሦስት ሳምንታት ልምምድ ስታሰራ ነበር። የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ፓትሪክ ማቤዲ ትናንት በሰጡት አስተያየት አንዳንድ ተጫዋቾች ጉዳት ላይ እንዳሉ ቢገልፁም የከፋ አስጊ ጉዳት ያለበት ተጫዋች እንደሌለ ጠቁመው ስብስባቸው መልካም የሚባል ልምምድ ሲሰራ እንደነበር በመግለፅ ጨዋታውን ወደ ሚያደርጉበት ሞዛምቢክ ቀድመው ገብተው ዐየሩን ለመልመድ እና ከሀገር ውጪ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን በቶሎ ለማቀናጀት እንዳሰቡ አመላክተዋል።
\"\"
አሠልጣኙ የፊታችን ሰኞ የመጨረሻ የተጫዋቾች ምርጫቸውን ይፋ እንደሚያደርጉ ሲጠበቅ በቀጣዩ ሳምንት ረቡዕ ከሞዛምቢክ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ለማድረግ ቀጠሮ እንደያዙም ተጠቁሟል።

በተያያዘ በኢትዮጵያ ምድብ የሚገኙት ጊኒ እና ግብፅ ለምድቡ 5ኛ ጨዋታ የተጫዋቾች ምርጫ በዚህ ሳምንት ይፋ አድርገዋል።