አዲሶቹ የዋልያዎቹ ተመራጮች ስለመጀመርያው የብሔራዊ ቡድን ጥሪያቸው ምን ይላሉ ?

በዘንድሮ የውድድር ዓመት ጥሩ ብቃት አሳይተው ለመጀመርያ ጊዜ ሀገራቸውን ለማገልገል ጥሪ ከቀረበላቸው ሦስት ተጫዋቾች ጋር ቆይታ አድርገናል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከማላዊ አቻው ጋር ላለበት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ 23 ተጫዋቾች በመጥራት በአዳማ ከተማ ዝግጅቱን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል። በስብስቡ ውስጥ ከሚገኙ ተጫዋቾች መካከል አቤል ማሙሽ ፣ አበባየሁ ሀጂሶ እና ፍራኦል መንግሥቱ ለመጀመርያ ጊዜ ሀገራቸውን ለመወከል የቀረበላቸው ጥሪ የፈጠረላቸውን ስሜት አጋርተውን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

\"\"

አቤል ማሙሽ (ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ)

ስለ ውድድር ዓመት ብቃቱ…

ውድድር ዓመቱ ጥሩ ነበር። እንደ ቡድን ጥሩ ነበርን፤ እንደሚታወቀው ከፍተኛ ሊግ ትንሽ ከበድ የሚል ውድድር ነው፤ ግን እንደ ቡድን ጥሩ ስለነበርን የተሳካ ዓመት አሳልፈናል።

የብሔራዊ ቡድን ጥሪ የፈጠረለት ስሜት…

መጠራቴን ስሰማ በጣም ነው ደስ ያለኝ ፤ ምክንያቱም አሁን እጠራለው ብዬ አልጠበቅኩም ነበር። በቆይታዬም ብዙ ልምድ አገኛለው ብዬ እጠብቃለሁ። በአጭር ጊዜ ቆይታም በቡድኑ በርካታ ልምድ ያላቸው ተጫዋች ስላሉ ብዙ ልምዶች እየወሰድኩ ነው።

በቀጣይነት ሀገሩን ለመወከል ያለው ዝግጁነት…

ዋነኛው ዕቅዴ ቀጣይ ዓመት በፕሪምየር ሊጉ ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ነው። አሁን ደግሞ የመጫወት ዕድሉን ካገኘው ጥሩ እንቅስቃሴ ለማድረግ እና በተከታታይ ሀገሬን መወከል ነው ያቀድኩት።

አበባየሁ ሀጂሶ (ወላይታ ድቻ)

ስለውድድር ዓመት ብቃቱ…

በግልም እንደ ቡድንም አሪፍ ጊዜ ነው ያሳለፍነው፤ በተለይም በግሌ የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረግኩበት ዓመት ነው። ይህንን ተከትሎም ለዋናው ብሔራዊ ቡድን መመረጥ ችያለው።

የብሔራዊ ቡድን ጥሪ የፈጠረበት ስሜት…

በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ነው ለዋናው ብሔራዊ ቡድን የተመረጥኩት ፤ ስሜቱ በጣም ደስ ይላል ምክንያቱም ሀገርህን ወክለህ በአፍሪካ መድረክ ከመጫወት በላይ የሚያስደስት ነገር የለም። በሀገሪቱ ካሉ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ልምምድ መስራት ብዙ ልምድ እንድትቀስም ዕድል ይፈጥርልሃል። በአጭር ጊዜ ቆይታዬም ልምዶች አግኝቻለው።

በቀጣይነት ሀገሩን ለመወከል ስላለው ዝግጁነት…

አሁን ለመጀመርያ ጊዜ ነው የተመረጥኩት የመጀመርያዬ ብቻ ሆኖ እንዲቀርም አልፈልግም። በክለብ ደረጃ ራሴን ጠብቄ በጥሩ አቋም በመጫወት ለረዥም ዓመታት ሀገሬን ማገልገል ነው ዕቅዴ። ይህ እንዲሆንም ጠንክሬ እሰራለሁ።

\"\"

ፍራኦል መንግሥቱ (ባህር ዳር ከተማ)

ስለውድድር ዓመት ብቃቱ…

ዘንድሮ ከመጀመሪያው ጀምሮ ጥሩ ጊዜ ነው ያሳለፍኩት ፤ እንደ ቡድንም አሰልጣኛችን በሚሰጠን መመርያ መሰረት ጥሩ የውድድር ዓመት ነው ያሳለፍነው። በግልም እንደ ቡድንም ጥሩ ጊዜ ነበረን። ይሄንን ጥሩ ብቃትም ቀጣይነት እንዲኖረው ጠንክሬ እሰራለሁ።

ዘንድሮ በተለየ በወጥነት ጥሩ ብቃት ላይ ስለመገኘቱ…

ዕድሉን ባለማግኘት ነው እንጂ ዘንድሮ የተለየ ነገር አልነበረም ፤ ማንም ተጫዋች ዕምነት ተጥሎበት ዕድሉ ከተሰጠው ራሱን ማሳየት ይችላል። ዘንድሮ ዕድሉን ስላገኘሁ በተቻለኝ መጠን ቡድኔን እያገለገልኩ ነው።

የብሔራዊ ቡድን ጥሪ ስለፈጠረበት ስሜት…

የተሰማኝ ስሜት እንዲህ ነው ብዬ መግለፅ አልችልም ፤ በጣም ትልቅ ደስታ ፈጥሮልኛል። ያለኝን ነገር ለሀገሬ ለብሔራዊ ቡድን ለመስጠት ዝግጁ ነኝ። አሁንም በጥሩ መንገድ እየተዘጋጀን ነው።

በቀጣይነት ሀገሩን ለመወከል ስላለው ዝግጁነት..

አሁን ያለኝን ብቃት ጠብቄ በማቆየት እና ራሴን በማሻሻል በቀጣይነት የስብስቡ አካል መሆን ነው የምፈልገው። በአካል እና በአዕምሮ ብቁ ሆኜ አቋሜን በመጠበቅ ከእግዚአብሄር ጋር አሳካዋለው ብዬ አስባለሁ። አሁን ሀገርህን መወከል ያለውን ስሜት አይቼዋለሁ። ይህን ነገር እንዲቀጥልም ቅድም እንዳልኩህ ጠንክሬ እሰራለሁ።

* በቀጣይ ከሌሎች ተጫዋቾች ጋር ያደረግነውን ቆይታ ይዘን እንመለሳለን።