ንግድ ባንክ የሰባት ተጫዋቾችን ውል አራዝሟል

ከከፍተኛ ሊጉ ወደ ትልቁ የሀገሪቱ የሊግ ዕርከን ያሳደጉ ሰባት ተጫዋቾች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውላቸው ተራዝሞላቸዋል።

በ2016 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ተሳታፊ ከሆኑ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው የአሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገዱ አዳጊው ክለብ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሌሎች የሊጉ ክለቦች ላቅ ባለ መልኩ በዝውውሩ የነቃ ተሳትፎን እያደረጉ ሲሆን ጎል ለጎን ደግሞ ውላቸው የተጠናቀቁ ነባር ተጫዋቾችን ኮንትራት እያራዘሙ ይገኛል። በዛሬው ዕለት ደግሞ ክለቡ ከከፍተኛ ሊጉ ሲያድግ የላቀ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሰባት ተጫዋቾች ውላቸውን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን በመገኘት ለተጨማሪ ዓመት ማራዘማቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
\"\"
የመሐል ተከላካዩ ፍቃዱ ደነቀ ውሉ የተራዘመለት ቀዳሚው ተጫዋች ነው። በድሬዳዋ ከተማ ፣ መቐለ 70 እንደርታ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ተጫውቶ ያሳለፈው ተጫዋቹ ወደ ቀድሞው ክለቡ ንግድ ባንክ ተመልሶ ክለቡን ማሳደግ መቻሉን ተከትሎ ውሉ ተራዝሞለታል።

\"\"

አላዛር መርኔ ውሉን ያደሰው ግብ ጠባቂ ነው። ከሀዋሳ ወጣት ቡድን ከተገኘ በኋላ በመቀጠል በኢኮስኮ ፣ ገላን ከተማ ፣ አርባምንጭ ከተማ (በውሰት) የተጫወተ ሲሆን በንግድ ባንክ ጥሩ የውድድር ዓመትን ማሳለፍ በመቻሉ ውሉን አድሷል።
\"\"
ዓመቱን በፕሪምየር ሊጉ ለለገጣፎ ለገዳዲ በግራ መስመር ተከላካይነት በመጫወት የጀመረው እና በአጋማሹ ንግድ ባንክን ተቀላቅሎ ዓመቱን ያገባደደው ኪሩቤል ወንድሙ ፣ በቅርቡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ጥሪ የደረሰው እና በከፍተኛ ሊጉ ለቡድኑ ግቦችን ሲያስቆጥር የነበረው አጥቂው አቤል ማሙሽ ፣ ከጉለሌ ክፍለ ከተማ ቡድኑን ተቀላቅሎ የነበረው ግብ ጠባቂው ፓላክ ቾል ፣ በገላን ተጫውቶ ያሳለፈው የተከላካይ አማካዩ ብሩክ እንዳለ እና የአጥቂ አማካዩ ብሩክ ብፁአምላክ ለተጨማሪ ዓመት ከክለቡ ጋር የሚቆዩ ተጫዋቾች ሆነዋል።