ዑመድ ኡኩሪ ራሱን ከብሔራዊ ቡድኑ ስላገለለበት ምክንያት ይናገራል…

👉 \”ኤምባሲ በተላከው ስብስብ ጭራሽ ስሜ አልተካተተም። ይህ ሁሉ ሲደረግ እኔ ግን ምንም መረጃ አልነበረኝም\”

👉 \”ምክንያቱን ማወቁን እፈልጋለው መብቱም አለኝ\”

👉 \”መምጣት ከፈለገ ወጪውን ራሱ ይሸፍን በማለት መናገራቸው አሳዝኖኛል\”

👉 \”ትልቁ ምክንያቴ አሜሪካ የመሄድ እና ያለመሄድ ጉዳይ አይደለም ፤ በአጠቃላይ አሰራሩ ግን ልክ አይደለም\”

አስቀድመን ባጋራናቹሁ መረጃ መሰረት ዑመድ ኡኩሪ ራሱን ከብሔራዊ ቡድን ማግለሉን ገልፀን ነበር። ዑመድ ከብሔራዊ ቡድኑ ራሱን ያገለለበትን ምክንያት አስመልክቶ ለሶከር ኢትዮጵያ የሰጠውን ምላሽ ከቆይታ በኋላ እናቀርባለን ባልነው መሠረት ከአሜሪካው ጉዞ ጋር የተገናኘውን ምክንያቱን በሰፊው ያብራራበትን ምላሽ እንደወረደ አቅርበነዋል።

\”እናንተም እንደሰማቹሁት ወደ አሜሪካ ይሄዳል የተባለው ስብስብ በጊኒ ጨዋታ ወቅት የነበሩ ተጫዋቾች መሆናቸው ተገልጿል። ለዚህም ለአሜሪካው ጉዞ አስቀድሞ ለተጫዋቾች በይፋ ጥሪ ከመደረጉ በፊት ለአሜሪካ ኤምባሲ የሚላክ ፎርም ለሌሎቹ ተጫዋቾች ሲላክ ለእኔ ፎርም አልተላከልኝም። ይባስ ደግሞ ወደ ኤምባሲ በተላከው ስብስብ ጭረሽ ስሜ አልተካተተም። ይህ ሁሉ ሲደረግ እኔ ግን ምንም መረጃ አልነበረኝም ፤ እንደማንኛውም ሰው ነው የምሰማው። ኦማን ሆኜ ከፌዴሬሽኑ የሚመለከታቸው አካላት ፎርም እንድሞላ የነገረኝ ወይም የደወለልኝ ሰው የለም ፤ አድራሻዬ ግን ነበራቸው። ከዚህ ቀደም ለነጥብ ጨዋታ እንደምታቁት በፊፋ ህግ መሰረት አንድ ክለብ ጨዋታው ሊደረግ ቀናት ሲቀረው ነው የመልቀቅ ግዴታ ያለበት ፤ ይህ ደግሞ ይታወቃል። እነርሱም ካለሁበት ሆነው የሚያስፈልገውን እየጠየቁኝ ቅድመ ሁኔታዎችን አመቻችተው ወደ ሀገሬ የምምጣው ዘግይቼ ቢሆንም የትም ሀገር ቀርቼ አላውቅም። አሁንም በሚያገኙኝ መንገድ ማግኘት ይችሉ ነበር። \’የአሜሪካ ጉዞ ሲሆን እንዴት ስም ዝርዝር ወደ ኤምባሲ ሲገባ ስሙን ዘለሉት ? ለምንስ ፎርም አላኩልኝም\’ ብዬ አሰብኩ።

 

የኦማን ሊግ አልቆ ወደ ሀገሬ ስመጣ ስለሚሆነው ነገር ምላሽ ፈልጌ በፌደሬሽን ውስጥ የሚመለከተው ግለሰብ ስደውል \’እስካሁን አልተላከህም እንዴ ?\’ ነው ያለኝ። \’አዎ በጊኒው ጨዋታ ስብስብ ውስጥ መሆኔ እየታወቀ ሌሎች ፎርም ተልኮ ስማቸው ኤምባሲ ገብቶ ለምን የእኔን መተው አስፈለገ ብዬ ጠየኩት ?\’ ጉዳዩን የያዘው ሰው ተረስቶ ይሆናል ብለው ፎርም ላኩልኝ ከዛ በኋላ ፎርም ሞላሁኝ በዛው ቀን ወዲያውኑ ለሚመለከተው ሰው ላኩለት። በዛ መሀል ግን ለአንዳንድ የማቃቸው ተጫዋቾች ስደውል በጁላይ አስራ አንድ ኢምባሴ እንደገቡ ነገሩኝ። ፎርምም እኔ ወደ ሀገሬ ከመግባቴ ከአስር ቀን በፊት እንደተላከላቸው ነገሩኝ። ተመልከት እነርሱ ፎርም ተልኮላቸው ኤምባሲ ሲገቡ እኔ ግን ገና ቀጠሮም አልነበረኝም ፤ የተነገረኝ ነገርም አልነበረም ኤምባሲም አልገባሁም። ነገሩን በፍጥነት ቀጠሮ ማስያዝ ሲገባቸው ቡድኑ ቪዛውን ከወሰደ ከሁለት ሳምንት በኋላ ደውለውልኝ \’ቀጠሮ እናስይዝልሃለን ክፍያው ደግሞ አንተ ነህ የምትፈፅመው\’ አሉኝ። \’ለምን ?\’ ስላቸው አስቸኳይ ስለሆነ ነው ገንዘቡ ይመለሳሀል አሉኝ። እኔም እሺ ብዬ በሀሳቡ ተስማማው ከዛ በኋላ ብጠብቅ ዝም ብለውኝ ሳምንት አለፈው።

ሲዘገዩብኝ \’ምክንያቱን ምንድነው ? ማወቅ እፈልጋለው መብቱም አለኝ\’ ብዬ ጠየቋቸው። እሺ ቆይ ላጣራ ብሎ በዛው ቀን ደወሉልኝ ማድረግ ያለብኝን እና ማክሰኞ ቀጠሮ መያዙን ነግረው ገንዘብ አስገባ አሉኝ። እኔም በፍጥነት ገንዘቡን አስገባሁኝ። ፌዴሬሽኑም ወደ አሜሪካ የሚጓዙትን ተጫዋቾችን ስም ዝርዝር ይፋ ሆነ። እኔም ሪፖርት አድርጉ በተባልነው መሠረት ሪፖርት በአግባቡ አድርጌ ወደ አዳማ ተጉዤ ልምምድ ጀመርኩ። ማክሰኞ ኤምባሲ ገባሁ ፤ እንደማንኛውም ሰው ግንዛቤ አልነበረኝም ፤ ቃለመጠይቅ ከጨረስክ በኋላ ቪዛ አገኘሁኝ። ቪዛዬን ይዤ ስወጣ \’ተመቷል ?\’ አለኝ የፌዴሬሽኑ ተወካይ \’አዎ\’ አልኩት \’እንኳን ደስ አለህ\’ አለኝ እና \’ለምን ነጩን ተቀበልክ ቢጫውን ወረቀት አትቀበልም ነበር ?\’ አለኝ። እዚህ ጋር ለቃለ መጠይቅ በፊት ለሚገቡት ሁሉ አስቀድሞ ግንዛቤ ይሰጣል ምን ማድረግ እንደሚገባ ፣ የኔ ጉዳይ ደግሞ ለየት ሰለሚል ቪዛውን ካገኘህ የሚሰጥህ ወረቀት ቢጫ እንዲሆን ንገራቸው ማለት ነበረባቸው። እኔ ምንም አላውቅም የሚሰጠው ቢጫ ወረቀት ይሁን ነጭ ወረቅት የተነገረኝ ነገር የለም። እኔ ነጭ ወረቀት ወሰድኩኝ። ለካ መሆን የነበረበት አስቸኳይ ስለሆነ ቢጫ ነበር መቀበል የነበረብኝ። በዚህ ምክንያት ነገሩ ተጓተተ። ነጭ ወረቀት ብቀበልም ዋናው ቪዛውን ማግኘት ስለሆነ እነሱም ሄደው ኤምባሲውን በማናገር ነገሩን ማስተካከል የሚችሉበት ዕድል ነበር ብዬ አስባለው። ምክንያቱም አስቸኳይ የብሔራዊ ቡድን ጉዳይ ስለሆነ በፍጥነት ወረቀቱን ማስቀየር ይችሉ ነበር። ግን እንደዛ አላደረጉም።

የፌዴሬሽኑ ሰው ረቡዕ ደወለልኝ ከዛ \’የተመታልህን ቪዛ አይቼዋለው ፤ ሄደህ DHI እይ\’ አለኝ ወድያውኑ እንዳላይ ልምምድ ላይ ስለነበርኩ በንጋታው ሐሙስ እሄዳለው ብዬ ጠዋት መጣው። ከሰዓት ቼክ ሳረግ \’DHl አልመጣም\’ አሉኝ አርብም ደወልኩኝ አልመጣም አሉኝ። ከዛ ደወለና \’ያንተ ጉዞ ቅዳሜ ነው ፤ ቪዛክ እስከ ዓርብ 12 ሰዓት ካልቀረበ ትኬት ቀኑ ያልፋል አለኝ።\’ ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ድጋሚ ደውሎ \’ያንተ ትኬት እስከ ቅዳሜ ዘጠኝ ሰዓት አራዝሜዋለው\’ አለኝ። ትኬቴ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ካልመጣ እንደማልሄድ ተገነዘብኩ ፤ ከደረሰ ደግሞ ማታ እበራለው። እንዳጋጣሚ ሰኞ ቪዛዬ እንደሚወጣ አረጋገጥኩኝ። ቅዳሜ ከቡድኑ ጋር አብሬ ባልጓዝ እንኳን ሰኞ መሄድ እችላለው ብዬ አሰብኩ ምክንያቱም ጨዋታው ረቡዕ ስለሆነ ሰኞ ብሄድ ማክሰኞ አሜሪካ ገብቼ ቡድኑን መቀላቀል እችል ነበር። ግን መሄድ እየቻልኩ ትኬቴን ለሰኞ አዙረው ማስተካከል አልፈለጉም። እኔ የተረዳሁት ከመጀመርያው ጀምሮ ስሜን አላካተቱትም ነበር። ቀጥሎ ፎርም ለሁሉም ሲላክ ለእኔ አልተላከም። አድራሻዬ ግን አላቸው። ከመጣው በኋላ ነው ደዋውዬ ያለውን ነገር ያወቅኩት። ይሄ ማለት እንድሄድ ፍላጎት አልነበራቸውም።

 

የተፈጠረውን ነገር ለጠበቃዬ ነገርኩት እና ያለውን ነገር አስረዳቸው በጣም የሚገርመው ደግሞ በጠበቃዬ በኩል \’መምጣት ከፈለገ ወጪው ራሱ ይሸፍን\’ በማለት መናገራቸው አሳዝኖኛል። እንዴት በግሉ መሄድ ይችላላል ይባላል። በአጠቃላይ ሀገርህን ወክለህ ስትጫወት ስሜቱ ልዩ ነው። የምወደው ከአስር ዓመት በላይ ያገለገልኩት ብሔራዊ ቡድን ለማገልገል ዝግጁ ነበርኩ። የሚሰሩት ሥራዎችም መታረም አለባቸው። አሁንም ቢሆን ምክንያቱም ማወቅ እፈልጋለሁ፤ ለኔ የመጣው ዕድል እስከ ሆነ ድረስ የመጠየቅ መብት አለኝ። ሁለተኛ ነገር ደግሞ ቪዛው ከተሰጠኝ በኋላ ለውድድሩ መድረስ እችል ነበር። ሀገርህን መወከል አትችልም ብለው አስበው ከሆነ በግልፅ ሊነገረኝ ይገባ ነበር። ትልቁ ምክንያቴ አሜሪካ የመሄድ እና ያለመሄድ ጉዳይ አይደለም። አሜሪካ ለመሄድ ብፈልግ በተለያዩ ሀገሮች እንደ መዞሬ ኤምባሲ ብገባ ቪዛ አገኛለው። ለእረፍት እንኳን አውሮፓ የምሄድባቸው አጋጣሚዎች አሉ ፤ ይህ ለኔ በጣም ቀላል ነው። የአሜሪካ ቪዛ የሰጠኝ እንኳን \’የት ሀገር ነው የምትጫወተው ?\’ ሲለኝ ኦማን ሊግ ስለው እዛው ቁጭ ብሎ ነው ጎግል ከፍቶ ፕሮፋይሌን የተጫወቱኩበትን ክለቦች አይቶ የተገረመው። ዋናው ቁም ነገር በግሌ ለመሄድ የአቅም ችግር የለብኝም ይህ የሀገር ጉዳይ ስለሆነ የመጣልኝ ዕድል መጠቀም ስላለብኝ ሀገሬንም ወክዬ መሄድ ስለፈለኩኝ እንጂ አሜሪካ ለመሄድ ጉጉት ኖሮብኝ አይደለም። በአጠቃላይ አሰራሩ ግን ልክ አይደለም። ይሄ ነገር አሁን እኔ ላይ ተፈፅሞ መቆም ስላለበት ነው። ለመናገር የተገድኩትም ግማሹን ለማስደሰት ግማሹንም ለማስከፋት አይለም። ወደፊት ታዳጊዎችስ እንዴት ሊሆን ነው ? ለወደፊቱ ትምህርት ሆኖ ማለፍ ስላለበት ነው።\”