ዑመድ ኡኩሪ ራሱን ከብሔራዊ ቡድን አገለለ

ያለፉትን አስራ ሁለት ዓመታት ሀገሩን ያገለገለው ዑመድ ራሱን ከብሔራዊ ቡድን ማግለሉን ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል።

ከጋምቤላ ፕሮጀክት ተገኝቶ በክለብ ደረጃ በመከላከያ(መቻል) የእግርኳስ ህይወቱን የጀመረው ዑመድ በኋላም በቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥሩ የእግርኳስ ዘመናት አሳልፎ በ2007 ወደ ግብፅ ሊግ አምርቶ አል-ኢትሀድ አሌክሳንድሪያን፣ ኢ ኢን ፒ ፒ አይ፣ ኤል-ኤንታግ አል-አርቢ፣ ስሞሀ እና አስዋን ሲጫወት ቆይቶ ወደ ሀገሩ በመመለስ ለሀዲያ ሆሳዕና መጫወቱ ይታወሳል። በዘንድሮ አመት ዑመድ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ኤዥያ በማቅናት ለኦማኑ አል-ሱዋይክ ክለብ በአሁኑ ወቅት እየተጫወተ ይገኛል።
\"\"
በ2006 በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች እና ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው በመሆን ያጠናቀቀው ዑመድ የኦማን ሊግ መጠናቀቁን ተከትሎ ለእረፍት በሀገር ቤት የሚገኝ ሲሆን እራሱን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማግለሉን ለሶከር ኢትዮጵያ አሳውቋል። ዑመድ ባስተላለፈውም መልዕክት \” ያለፉትን ከአስር ዓመታት በላይ ሀገሬን በምትፈልገኝ ወቅት ሁሉ በመገኘት ሳገለግል ቆይቻለው። ለሀገር መጫወት ትልቅ ክብር ነው። በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ። እስከ ዛሬም ሲደግፉኝ ሲያበረታቱኝ ለቆዮት ሁሉ ምስጋናዬን አቀርባለው። ሀገሬ ማገልገል ብፈልገም በአንዳን ነገሮች ምክንያት ራሴን ለማግለል ወስኛለው\” በማለት ዑመድ ኡኩሪ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል።
\"\"
ዑመድ ከብሔራዊ ቡድን ራሱን ለማግለል ያበቃውን ምክንያት ለሶከር ኢትዮጵያ በብቸኝነት የሰጠውን ሀሳብ ከቆይታ በኋላ የምናቀርብ ይሆናል።