አንጋፋው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ዳግም ወደ እግር ኳስ ተመለሰ

ቀደም ብሎ ጫማውን መስቀሉን ይፋ ያደረገው ትውልደ ኢትየጵያዊ ዳግም ወደ እግር ኳስ መመለሱን አስታወቀ።

ቀደም ብሎ ጫማውን ሰቅሎ የነበረው የሰላሳ ሰባት ዓመቱ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሁለገብ ተጫዋች አሚን አስካር ከስፕሪንት ጄሎይ የተባለ ክለብ ጋር የአጭር ጊዜ ቆይታ ለማድረግ ወደ እግር ኳሱ ተመለሰ። ለመጨረሻ ጊዜ ሞስ በተባለ እግር ኳስ በጀመረበት ክለብ ቆይታ የነበረው ይህ ተጫዋች አሁን ደግሞ በኖርዌይ ሶስተኛ የሊግ እርከን ተሳታፊ ለሆነው ክለብ ለአጭር ጊዜ ቆይታ ፊርማውን አኑሯል።
\"\"
ፊርማውን ካኖረ በኋላ ከአዲሱ ክለቡ ጋር የመጀመርያውን ጨዋታ ያደረገው ይህ ተጫዋች ወደ እግር ኳስ መመለሱ አስመልክቶ አስተያየቱን ሰጥቷል። በአስተያየቱም \” አሰልጣኞቹ Vegard Gildseth Andersen እና Vegard Haslerud አብሮ አደግ ጓደኞቼ ናቸው፤ እዚህ መምጣቴም ደስተኛ አድርጎኛል። በትልቅ ደረጃ መጫወት በቃኝ ብያለው፤ ይህ ማለት ግን አቁምያለው ማለት አደለም\” ብሏል።

በ2005 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከናይጀርያ ጋር ለሚያደርገው የብራዚል ዓለም ዋንጫ ማጣርያ ለመጫወት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በአንዳንድ የወረቀት ጉዳዮች ምክንያት ሳይጫወት የተመለሰው ይህ አንጋፋ ተጫዋች ከዚህ በፊት ሞስ፣ ፍሬድሪክስታድና ብራንን ጨምሮ በስምስት ክለቦች ተዘዋውሮ መጫወቱ ይታወሳል። በእግርኳስ ሂወቱም 405 ጨዋታዎች አከናውኖ 50 ግቦች ማስቆጠር የቻለ ተጫዋች ነው።
\"\"
በተያያዘ ዜና ጎን ለጎን ወደ ማሰልጠኑ ገብቶ የነበረው የሰላሣ ዘጠኝ ዓመቱ የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የመስመር ተጫዋች የሱፍ ሳላፍ በአሁኑ ወቅት Rinkeby United ለተባለ በስዊድን ታችኛው ዲቪዝዮን የሚሳተፈው ቡድን ውስጥ በመጫወት ላይ ይገኛል።

በእግር ኳስ ሂወቱ ለአስር የተለያዩ ክለቦች የተጫወተይ ይህ ፈጣን የመስመር ተጫዋች ኢትዮጵያን ወክሎ አስራ ሁለት ጨዋታዎች በማድረግ ሁለት ግቦች ማስቆጠሩ ይታወሳል።