ከአሜሪካ በዲሲፕሊን ጥሰት የተመለሱት ተጫዋቾች…

👉\”የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ\” ብርሀኑ በቀለ

👉ዮሴፍ ታረቀኝ በጉዳዩ ላይ መልስ ሳይሰጠን ቀርቷል…
\"\"
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአሜሪካን ሀገር የጉብኝት የወዳጅነት ጨዋታዎችን እያደረገ ይገኛል። ብሔራዊ ቡድናችን ወደ ስፍራው አምርቶ የመጀመሪያ የወዳጅነት ጨዋታውን ከጉያና ብሔራዊ ቡድን ጋር አድርጎ 2ለ0 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ በጨዋታ ዕለት የመስመር ተከላካዩ ብርሀኑ በቀለ እና የመስመር አጥቂው ዮሴፍ ታረቀኝ በፈፀሙት ያፈነገጠ የእርስ በእርስ ጥል የተነሳ በማግስቱ ፌዴሬሽኑ ሁለቱም ተጫዋቾች ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ ውሳኔ በማስተላለፉ መመለስ መቻላቸው ይታወሳል። በቀጣይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የሁለቱን ተጫዋቾች ጉዳይ ካጠራ በኋላ ቅጣት ሊያስተላልፍ እንደሆነ ባደረግነው ማጣራት ለማወቅ የቻልን ሲሆን በጉዳዩ ዙሪያ ሁለቱን ተጫዋቾችን ለማናገር ሙከራን አድርገን የአዳማ ከተማው የመስመር አጥቂ ዮሴፍ ታረቀኝ \”አሁን ምንም ማለት አልፈልግም። ውሳኔም ካለ ውሳኔው ይሰጥና ከዛ በኋላ ሀሳቤን እሰጣለው\” በማለት የተናገረ ሲሆን አዲሱ የሲዳማ ቡና ፈራሚ ብርሀኑ በቀለ ግን ስለ ጉዳዩ ለሶከር ኢትዮጵያ ማብራሪያ የሰጠ ከመሆን ባለፈ ለፈፀመው የዲሲፕሊን ጥሰትም ይቅርታውን በተከታዩ መልክ ገልጿል።
\"\"
\”በእርግጥ እንዲህ ይከሰታል ብዬ አላሰብኩም ፤ የቀን ጉዳይ ሆኖ ይሄ ነገር ተከሰተ። በእግር ኳስ አለም እንደዚህ አይነት ግጭት ይኖራል። ይሄ እንዳለ ሆኖ በእርግጥ ልጁ ባህሪው በጣም አስቸጋሪ ነው። እንኳን ከእኔ ጋር ይቅር እና ሲኒየር ተጫዋቾችን የመናቅ አይነት ባህሪ አለበት። በአጠቃላይ ስለ እርሱ ባህሪ ላወራ ሳይሆን ምንድነው ኬዙ በአጋጣሚ የጌም ቀን ነበርና ከጉያና ጋር ልንጫወት ሜዳ ተገኝተን መሐል ገብ ላይ ነው ንክኪው የተነሳው። ኳስ ተነክቶበት አልገባም አይነት ነገር ብሎ ለሲኒየሮቹ ሲመልስ ግባ አልገባም በሚል ሰጣ ገባ ውስጥ ገባንና ይሄ ነገር እስከ መልበሻ ቤት ድረስ ግጭቱ ሰፋ እና የመያያዝ ነገር መጣ። ፀቡ በዚህ ነበር የተነሳው። ልጁ የሚገርመው የዛን ቀን ቲክቶክ ላይ ቤስት 11 ዲኤስቲቪ የዓመቱ ያወጣው አለ ስሜን እየጠራ ያልሆነ ሀሳብ ያነሳል ፤ ተጫዋቾችን የማቅለል ነገር አለበት እና አንተ ልጅ እረፍ ብዬ ነግሬውም ነበር። በአጠቃላይ ይሄ ሁሉ ነገሮች ተደምሮብኝ ሜዳ ላይም ሆኖ ያልሆነ ነገር ሲያወራ ምላሹም ንግግሩም ያስጠላል። በዛም ነበረ ግጭቱ የተነሳው መጨረሻ ላይ ጨዋታው አለቀ ለሊት አካባቢ ነበር ጨዋታው ያለቀው ከእራት መልስ ወደ ሩማችን ተመለስን ከተመለስን በኋላ ይቅርታ ሰዎቹን መጠየቅ ፈልጌ ነበር ላወራቸውም ኬዙን ድካም ላይ ስለነበሩ በእራትም ፕሮግራም ትንሽ አምሽተን ነበር። በዚህ መሐል ደግሞ ሻንጣህን አዘጋጅ መልዕክት ተላለፈብኝ። ወደ ሀገር ቤት እንድትመለሱ የሚል። እሺ አልኩኝ ማውራትም ሳልችል ቀጥታ ተመለስኩኝ። በተፈጠረው ሁሉ ጓደኞቼ ተጫዋቾችን ፣ ኮቺንግ ስታፉን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽንን በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ ፤ በጣም አዝኛለሁ።\”