ሀድያ ሆሳዕና ሁለት ተጫዋቾችን አስፈርሟል

በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የሚመሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች ሁለት ተጫዋቾችን ሲያስፈርሙ የአንድ ተጫዋችን ውል አራዝመዋል።

በአዲሱ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ መሪነት በክለቡ መቀመጫ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን አዳዲስ እና ነባር ተጫዋቾችን በጣምራ በመያዝ እየሰሩ የሚገኙት ሀድያ ሆሳዕናዎች ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርሙ የአንድ ተጫዋቾችን ውል አራዝመዋል።

የኋላሸት ሠለሞን አዲሱ የክለቡ ፈራሚ ሆኗል። የቀድሞው የዲላ ከተማ እና ኢኮስኮ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች የተጠናቀቀውን ዓመት በፕሪምየር ሊጉ ከወልቂጤ ከተማ ጋር በመጫወት አሳልፎ ለቀጣዩ ዓመት በሀድያ ሆሳዕና ለመጫወት የተሰጠውን የሙከራ ዕድል በአግባቡ ማጠናቀቁን ተከትሎ ክለቡን በሁለት ዓመት ውል ተቀላቅሏል። ሌላኛው ፈራሚ በክረምት ወራት በሆሳዕና ከተማ በሚደረገው የያሆዴ ዋንጫ ላይ ሲጫወት የነበረው አጥቂው ፀጋአብ ግዛው ክለቡን የተቀላቀለ ሌላኛው ተጫዋች ነው።

ክለቡ ከሁለቱ ፈራሚዎች በተጨማሪ የአጥቂውን ዘካርያስ ፍቅሬን ኮንትራትም አራዝሟል።