“ተጫዋቾቻችን ያገኙትን ዕድል አልተጠቀሙም እንጂ ማሸነፍ እንችል ነበር” ብርሃኑ ግዛው

በሴካፋ የቻምፒየንስ ሊግ ማጣሪያ የፍፃሜ ጨዋታ የተረቱት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ተከታዩን የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ሰጥተውናል።

ጨዋታው እንዴት ነበር?

እውነት ለመናገር ጨዋታው ጥሩ ነበር። በዳኝነትም ከባለፈው ጨዋታ የተቻሉ ነገሮች ነበሩ። ተጫዋቾቻችን ያገኙትን ዕድል አልተጠቀሙም እንጂ ማሸነፍ እንችል ነበር። ደግሞ ተጫዋቾቼ ባለፈው 120 ደቂቃ ነው የተጫወቱት። በምድብ ደግሞ 6 ጨዋታ ነው የተጫወቱት። ይህ ድካም ፈጥሯል። የሆነው ሆኖ በእንቅስቃሴ ረገድ የምችለውን ነገር አድርገናል።

ምን አይነት የጨዋታ ዕቅድ ይዛችሁ ነበር ወደ ሜዳ የገባችሁት?

ከእቅድ ጋር ተያይዞ በቡድኔ ኳስ የሚችሉ ተጫዋቾች ስላሉ ኳስ ይዘን ነው የምንጫወተው። በአብዛኛው ግን ማጣቃት ነበር ፍላጎታችን። በጨዋታው እንደውም 6 አጥቂዎችን ተጠቅመናል። በዚህም የጎል ዕድሎች ተፈጥሮ ነበር። ግን አልሆነም።

ተጋጣሚያችሁን እንዴት አገኘከው?

ተጋጣሚያችን እጅግ በጣም ወጣቶች ናቸው። ታጋዮች እና ብዙ ጎል ያልገባባቸው ናቸው። እርግጥ እኛ ፈትነናቸዋል። ብዙ የግብ ዕድሎችን ፈጥረን ነበር። ግን በአጠቃላይ ዲሲፕሊን ያለው ጠንካራ እና ታታሪ ወጣቶች ያሉበት ቡድን ነው።

ግብ ፊት የነበረው ክፍተት ከምን የመጣ ነው?

ግብ ፊት በተወሰነ መልክ መጓጓቶች ነበሩ። ጨዋታውን አሸንፈን እንወጣለን የሚል ሀሳብ ነበረ። ይሄ ትንሽ ተጫዋቾቼ ላይ ጉጉት ፈጥሯል። ይህ ነገር ነው የፈተነን እንጂ የግብ ዕድሎችን በበቂ ሁኔታ ፈጥረናል።


ቡድኑ ላይ ከሥነ-ልቦና ጋር ተያይዞ ክፍተት ያለ ይመስላል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ምን ትላለህ
?

ተጫዋቾቼ የሚችሉትን አድርገው ተዘጋጅተው ነበር። ጨዋታዎች ላይ ከፍተኛ ክፍተት ነበረብን ፤ ይህንን ግን ከጨዋታ ጨዋታ አርመን መጥተን ትናንት ያለውን ነገር ለማስተካከል ሞክረናል። ምንም ማድረግ አይቻልም ፈጣሪ አልፈቀደም ዋንጫ ማምጣት አልቻልንም። ግብ አስቆጥረን ዋንጫ ባናመጣም ተጫዋቾቼ ያደረጉት እንቅስቃሴ ቀላል አይደለም። ሁለት ጊዜ 120 ደቂቃ ተጫውተዋል። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያዊያን በአካልም በስነ-ልቦናም እንደዚህ ረጅም ሰዓት ታግሎ መጫወት ይቀራቸዋል። ዞሮ ዞሮ የተሸነፍነው በመለያ ምት ነው። ፍፁም ቅጣት ምት ደግሞ የዕድልም ጉዳይ ነው ብዬ ነው የማስበው። በመጨረሻ ተጫዋቾቼን፣ የአሠልጣኝ ቡድን አባላት፣ እዚህ የነበረውን ደጋፊ እና የስፖርት ማኅበሩ ፕሬዝዳንት በአካል መጥተው ስለተመለከቱን እጅግ አድርጌ አመሰግናለው።