የቡናማዎቹ ተጫዋች ለዋልያዎቹ ጥሪ ቀርቦለታል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለግብፁ ጨዋታ ዛሬ ልምምዱን ሲጀምር ሦስት ተጫዋቾች በልምምዱ ያልተገኙ ሲሆን አንድ አዲስ ተጫዋችም ቡድኑን ተቀላቅሏል።

በአይቮሪኮስት አስተናጋጅነት ለሚከናወነው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በሚደረግ የምድብ የማጣሪያ ውድድር ሲሳተፍ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቀሪ አንድ ጨዋታ እየቀረው ከምድብ መውደቁን ማወቁ ይታወሳል። ብሔራዊ ቡድኑ ከግብፅ ጋር ላለበት የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ በማቅረብ ከትናንት በስትያ የተሰባሰበ ሲሆን በትናንትናው ዕለት ልምምዱን ይጀምራል ተብሎ ቢጠበቅም ልምምድ ሳይሰራ ቀርቷል።

በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የመጀመሪያ ልምምዱን እየሰራ የሚገኘው ቡድኑም ጥሪ ካቀረበላቸው ተጫዋቾች መካከል ሽመልስ በቀለ፣ ቢኒያም በላይ እና ምኞት ደበበ በልምምዱ ላይ እንደሌሉ ሶከር ኢትዮጵያ በስፍራው ተገኝታ ተመልክታለች።

ቀድሞ ጥሪ ከደረሳቸው 23 ተጫዋቾች ውጪ ደግሞ የኢትዮጵያ ቡናው የመሐል ተከላካይ ራምኬል ጀምስ የመጀመሪያ የብሔራዊ ቡድን ጥሪ ደርሶት ቡድኑን ተቀላቅሎ ልምምድ እየሰራ እንደሚገኝ አስተውለናል።