ሻሸመኔ የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቋል

ሻሸመኔ ከተማ ስብስቡን በዝውውር ማጠናከር ሲቀጥል የቡድኑን ረዳት አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች ውል አራዝሟል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተሳትፎ ጊዜውን የፊታችን ዓርብ ወላይታ ድቻን በመግጠም ውድድሩን የሚጀምረው ሻሸመኔ ከተማ በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት በርካታ ተጫዋቾች በመቀላቀል ዝግጅቱን ሲሰራ የሰነበተ ሲሆን በትላንትናው ዕለት ከፈረመው ያሬድ ዳዊት በተጨማሪ ሌሎች ተጫዋቾችን አስፈርሟል።

ክለቡን የተቀላቀለው አዲሱ ፈራሚ አማካዩ ሀብታሙ ንጉሴ ሆኗል። የቀድሞው የባህር ዳር ከተማ ፣ ወልዲያ እና ጅማ አባ ጅፋር ተጫዋች ያለፉትን ሁለት ዓመታት በወላይታ ድቻ ካሳለፈ በኋላ ቀጣዩ ክለቡ ሻሸመኔ ሆኗል። በአርሲ ነገሌ በግብ ጠባቂነት ሲጫወት የምናውቀው አባቱ ጃርሶ ሌላኛው የቡድኑ አዲስ ፈራሚ ነው።

ከአዳዲስ ፈራሚዎቹ በተጨማሪ ክለቡ የረዳት አሰልጣኙ በቀለ ቡሎ እና የግብ ጠባቂ አሰልጣኙ የቀድሞ የሀዋሳ ከተማ ግብ ጠባቂ የነበረውን አጥናፉ ታደሰን ውል ጨምሮ በክለቡ ወሳኝ ከነበሩ ተጫዋቾች መካከል የአብዱልከሪም ቃሲም እና ኤቢሳ ከድርን ውል ስለማደሱ ተገልጿል።