ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ከሦስት ዓመታት በኋላ የመክፈቻ ጨዋታውን በድል ተወጥቷል

በምሽቱ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና በኤርሚያስ ሹምበዛ ድንቅ ጎል ሲዳማ ቡናን 1-0 መርታት ችሏል።

ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ የጀመረው ጨዋታ ቀድሞ የሲዳማ ቡና መልሶ ማጥቃት አስፈሪነትን አስመልክቶናል። 6ኛው ደቂቃ ላይ የፊልፕ አጃህ እና ቡልቻ ሹራ ጥምረት የፈጠረው ያለቀለት የመልሶ ማጥቃት ዕድል በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነበር። የሜዳውን ስፋት ተጠቅመው በኳስ ቁጥጥር ቀስ በቀስ ጫና መፍጠር የጀመሩ ቡናዎች ቀዳሚ አደጋዎቻቸው ከቆመ ኳስ የተገኙ ነበሩ። 15ኛው ደቂቃ ላይ ወልደአማኑኤል ጌቱ ከማዕዘን ምት በተነሳ ኳስ ያደረገው ሙከራ ተጨርፎ ሲወጣ ከደቂቃ በኋላ ደግሞ የብሩክ በየነ የቅጣት ምት ቡልቻ ሹራ ራሱ ላይ እንዲያስቆጥር ምክንያት ለመሆን ተቃርቦ ነበር።

ጉሽሚያዎች እየታዩበት እና የእንቅስቃሴ ፍጥነቱ ዝግ እያለ በዘለቀው አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡና የማጥቃት የበላይነቱን ይዞ መዝለቅ የቻለ ሲሆን በተለይም ጫላ ተሺታ የተሰለፈበት የቡድኑ የቀኝ ክፍል የተሻላ የጥቃት መነሻ ሆኖ ታይቷል። ዕረፍት ሲቃረብ ተጋጣሚያቸውን በመቆጣጠር እየተሻሻሉ በታዩት ሲዳማ ቡናዎች በኩል ይስሀቅ ካኖ ከግብ ጠባቂው በረከት አማረ የነጠቀውን ኳስ አሻግሮት ፍሊፕ አጃህ 43ኛው ደቂቃ ላይ በግንባር ያደረገው ሙከራ ለግብ የቀረበ ነበር።

በዕረፍት መልስ ኢትዮጵያ ቡና ከፊልፕ አጃህ ጋር ግጭት አስተናግዶ የነበረው በረከት አማረን በእስራኤል መስፍን ቀይሮ ጀምሯል። በእንቅስቃሴ ከቀደመው አጋማሽ ዝግ ያለ አጀማመር ቢታይም ጠንከር ያሉ የግብ ሙከራዎች ተስተውለዋል። 53ኛው ደቂቃ ላይ በልቻ ሹራ ከግራ መስመር ወደ ውስጥ በመግባት ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሲያደርግ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ በተቃራኒው ጎል ጫላ ተሺታ በቀኝ በተመሳሳይ አኳኋን ያደረገው ሙከራ ወደ ላይ ተነስቷል። በእንቅሳሴ ሲዳማዎች ከግብ ክልላቸው ኳስ በአግባቡ ማራቅ ሳይችሉ ጫና ውስጥ እየገቡ ሲታዩ 59ኛው ደቂቃ ላይ በተመሳሳይ የብሩክ በየነን የማዕዘን ምት ቢጨርፉም ኤርሚያስ ሹምበዛ ከሳጥን ውጪ አግኝቶ አክርሮ በመምታት ለዓይን ሳቢ ጎል አስቆጥሮ ኢትዮጵያ ቡናን መሪ ማድረግ አድርጓል።

ከግቡ በኋላም የኢትዮጵያ ቡና ጥቃት ፍጥነት ከፍ ብሎ ሲታይ መክብብ ደገፉ የበፍቃዱ ዓለማየሁ እና ጫላ ተሺታን ያለቀላቸው የግብ ዕድሎች ባያድን ውጤቱ በደቂቃዎች ልዩነት ሊሰፋ ይችል ነበር። በቀጣይ ደቂቃዎች ሲዳማዎች የደረሰባቸውን ጫና አርግበው በቆሙ እና ቀጥተኛ ኳሶች ምላሽ ለመስጠት ሲሞክሩ የታየ ቢሆንም የኢትዮጵያ ቡናዎች ከኳስ ውጪ ከፍ ያለ ጫና በመፍጠር የማስጣል አጨዋወት ነገሮችን ቀላል አላረገላቸውም። ይልቁኑም ጨዋታው ወደ ማብቂያው ሲቃረብ ኢትዮጵያ ቡናዎች ሲዳማን ከከባድ ሙከራዎች በማገድ እና ጨዋታውን በመቆጣጠር ረገድ ተሳክቶላቸው የ1-0 መሪነታቸውን በማስጠበቅ አሸንፈው ወጥተዋል።

አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ የተወሰደባቸውን ብልጫ በሁለተኛው አጋማሽ ለማሻሻል ቢሞክሩም በጎል መቀደማቸውን አንስተው እንደመጀመሪያ ጨዋታ መጥፎ እንዳልነበሩ አብራርተዋል። ዘጠና ደቂቃ ከፍ ባለ ጫና መጫወታቸውን ያነሱት አሰልጣኝ ኒኮላ ካቫዞቪች በበኩላቸው ወጣት ተጫዋቾቻቸውን እና ደጋፊዎቻቸውን አመስግነው ከመጀመሪያው 20 ደቂቃ በኋላ ሜዳ ውስጥ የእሳቸው ቡድን ብቻ እንደነበር በመግለፅ ከጨዋታው እንቅስቃሴ ይልቅ ሦስት ነጥብ ማግኘት የበለጠ ትርጉም እንዳለው ተናግረዋል።