ለአፍሪካ ሴት ኢንስትራክተሮች ራባት ላይ ሲሰጥ የነበረው ሥልጠና ተጠናቋል

በኢትዮጵያዊው የካፍ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ እና ሌሎች ሁለት የአህጉሪቱ ባለሙያዎች በአሰልጣኝነት የተሳተፉበት የአፍሪካ ሴት ኤሊት ኢንስትራክተሮች ሥልጠና ተጠናቀቀ።

ካፍ በአህጉሪቱ የሚገኙ ሴት ኢንስትራክተሮች በክፍል ውስጥ እና በተግባር ራሳቸውን በማብቃት ሌሎች ሙያተኞችን በይበልጥ እንዲያፈሩ ብቃታቸውን እንዲያሻሽሉ በሚል መርህ በሞሮኮ ራባት ከተማ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ለተወጣጡ ወደ 16 የሚደርሱ ሴት የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተሮችን ለስምንት ተከታታይ ቀናት ሲያሳትፍ  የነበረው ሥልጠና በዛሬው ዕለት ተጠናቋል። በየሦስት ዓመቱ የሚሰጠውን ይህን ስልጠና ራቫት ላይ ተገኝተው የሰጡት ኢትዮጵያዊው የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ከናሚቢያዊቷ ጃኪ ቺፓንዳ እና የአይቮሪኮስት ዜግነት ካላት ክሌመንቲ ቱሬ ጋር በጋራ በመሆን ነው መስጠት የቻሉት።

ለቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ሥልጠናውን የወሰዱ ኢንስትራክተሮች ወደ ሀገራቸው ተመልሰው እንዲሁም በአፍሪካ የተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ሥልጠናዎችን በብቃት እንዲያስተምሩ ፣ በተሻለ ደረጃ እንዲያበቁ ዓላማውን አድርጎ በተዘጋጀው በዚህ መድረክ ኢትዮጵያዊው ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ በአሰልጣኝነት ሲሳተፉ ሌላኛዎቹ ኢትዮጵያዊያን የካፍ የሴቶች እግርኳስ ዲቪዥን ኃላፊዋ መስከረም ታደሰ በሥልጠና አስተባባሪነት የላይቤሪያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ በበኩሏ በሰልጣኝነት ተሳትፈውበታል።

ለሴት ኢንስትራክሮች የሚሰጠው ሥልጠና ዛሬ መጠናቀቁን ተከትሎ ከአንድ ሳምንት በኋላ ደግሞ ለወንድ ኢንስትራክተሮች ስልጠናው እየተሰጠ የሚቀጥል ይሆናል። በቀጣይም ኢትዮጵያዊያን አዳዲስ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት የአዳዲስ ኢንስትራክተሮች የስልጠና መርሐ-ግብር በቅርቡ በካፍ ደረጃ እንደሚኖርም ዝግጅት ክፍላችን ለማወቅ ችላለች።