አፄዎቹ አይቮሪኮስታዊ ተከላካይ አስፈርመዋል

ፋሲል ከነማዎች ቀደም በማለት በዝውውር ዝርዝር ውስጥ አካተውት የነበረውን አይቮሪስታዊ የመሐል ተከላካይ ወደ ስብስባቸው በይፋ አካተዋል።

የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታቸውን ከሀዋሳ ከተማ ጋር አድርገው 3-3 በሆነ የአቻ ውጤት የፈፀሙት ፋሲል ከነማዎች የዝውውር መስኮቱ ከመዘጋቱ በፊት ስሙን በዝርዝር ውስጥ አካተውት የነበረውን አይቮሪስታዊውን የመሐል ተከላካይ ዠርሚን ፒዮት ዶህን ዝውውር ፈፅመዋል።

የእግር ኳስ ህይወቱን በአብዛኛው ከሀገሩ ውጪ በቤኒን ሱፐር ሊግ ክለብ በሆኑት ኤ ኤስ ቪኦ እንዲሁም ደግሞ ድራጎን በተባሉ ቡድኖች ውስጥ ተጫውቶ ያሳለፈው ተጫዋቹ በአንድ አጋጣሚ በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ላይ ለፋሲል ከነማ ተሰልፎ የተጫወተው ተከላካዩ ከሰሞኑ የነበሩበትን የወረቀት ሥራዎች በማጠናቀቁ በቀጣዩ የሊግ ጨዋታ ፋሲል ከነማ ኢትዮጵያ መድንን ሲገጥም የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታውን ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ሶከር ኢትዮጵያ ለማወቅ ችላለች።

ክለቡ ከውጪ ዜጋ ተጫዋቹ በተጨማሪ ከሰሞኑ ልዑልሰገድ አለማየሁ የተባለ ከዚህ ቀደም በአዳማ ተስፋ ቡድን ሲጫወት የነበረ ታዳጊ መቀላቀሉ ይታወሳል።