የአሰልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 2-2 ሀምበርቾ

“ጎሎችን ማግባት በምንችልበት ሰዓት ትንሽ ስለ ዘገየን አቻ ወጥተናል” አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ

“ለእኛ አንድ ነጥቡ መጥፎ አይደለም” አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ

አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ – አዳማ ከተማ

ስለ ጨዋታው…

“ሀምበሪቾ ጥሩ ተጫዋቾች ያሉበት እና ጎበዝ አሰልጣኝ ፣ ጥሩ ቡድን ነው። እንደ ማንኛውም ቡድን ከሀምበሪቾ ጋር የነበረን ነገር ጠንካራ ዝግጅት ስለነበረን ውጤቱ መጥፎ አይደለም።”

ቡድኑ ላይ ስለ ነበረው ጠንካራ ጎን…

“ከፊት ያሉት ተጫዋቾች ጥንካሬያቸው ነበር ፣ ከኋላም ያሉት እንደ ቡድን ነው የተጫወቱት ይሄ ነው ብዬ ዲፓርትመንቱን መከፋፈል አልችልም ፣ እንደ ቡድን መነሳሳታቸው ጥሩ ነበር ግን በተነሳሳንበት ሰዓት ፣ ጎሎችን ማግባት በምንችልበት ሰዓት ትንሽ ስለ ዘገየን አቻ ወጥተናል።”

በተደጋጋሚ እየታዩ ስላሉ ስኬታማ የተጫዋች ቅያሪዎች…

“አሰልጣኝ አይደለህ ፣ ከአምናው የምትማራቸው ነገሮች አሉ ፣ አምና ብዙ ስህተቶች ነበሩ። አሰልጣኝ ስትሆን ደግሞ ከእያንዳንዱ ጨዋታ የምታስተካክለው ነገር አለ ነገ ደግሞ ስህተቶች በቅያሪ ሊኖር ይችላል እና የዛሬው ቅያሪ እንደተለመደው ነው ውጤታማ ነበር።”

አንድ ነጥብ ብቻ ከጨዋታው ስለ ማግኘታቸው…

“ከዕረፍት በፊት ከነበረን ነገር አንፃር አንድ ነጥብ በቂ ነው ብዬ አላስብም ፣ ግን ሀምበሪቾ ማወቅ ያለብን በጣም ጠንካራ ቡድን ነው ፣ እነርሱንም ጥንካሬያቸውን አለመግለፅ ንፉግነት ነው።”

ዊሊያም ለጀሚል ፣ ጀሚልም በተመሳሳይ አቀብሎ ግቦች እንዲቆጠሩ ስለ ተደረጉበት መንገድ…

“በአጋጣሚ ብዙ ጊዜ እንደዚህ አይነት ጎል ሲገባ ሰርተን ነው ጎሉ ሲገባ በአጋጣሚም ነው ልልህ አልችልም። እዛ ጋር የሚደርሱበትን ነገር ነው እንደ አሰልጣኝ የምታሳየው ነገም ተጨራርፎ ሊገባ ይችላል ግን እዛ ጋር በተቻለ መጠን ሲሄዱ እንዳይቸኩሉ ነው ልምምድ ሲሰሩ የነበረው አልቸኮሉም በዛም ነው ጎል ሊሆን የቻለው።”

አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ – ሀምበርቾ

ስለ ሁለቱ የጨዋታ አጋማሾች …

“ጨዋታው የመጀመሪያው አርባ አምስት ጥሩ ነው። በሁለተኛው ትንሽ ጎሉን ካገባን በኋላ አፈግፍገን ነበር እና ይሄ ደግሞ ግብ እንዲቆጠርብን ሆኗል።”

ማፈግፈጉ ውጤት ለማስጠበቅ ስለ መሆኑ…

“ያም ብቻ ሳይሆን ምንአልባትም ቡድኑ ነጥብ ይፈልጋል ፣ ያንን ነጥብ በአሸናፊነት ይዘን ለመሄድ በማሰብ ነው ግን ወደፊት ገፍተን እንድንጫወት መልዕክት እያስተላለፍከኝ ነበር። ተጫዋቾቹ ጋር የስነ ልቦና ጉዳይ አለ ነጥብ ለማግኘት ፣ ይሄ ነገር ትንሽ ጎድቶናል።”

ስለ ዛሬው አንድ ነጥብ እና ስለ ቀጣይ ጨዋታዎች…

“ዛሬ ብናሸንፍ ጥሩ ነበር ፣ አንድ ነጥብ ደግሞ ተነሳሽነት ይጨምራል ፣ አሁን ደግሞ በስነ-ልቦናው ረገድ ከአሁን በኋላ ስትመጣ ደግሞ ነጥብ እስከ አሁን ስላላገኘን ለእኛ አንድ ነጥቡ መጥፎ አይደለም።”