ሪፖርት | የሳምንቱ ምርጥ ጨዋታ አቻ ተጠናቋል

ብርቱ ፉክክር የተደረገበት እና ለተመልካች እጅግ ማራኪ የነበረው የኢትዮጵያ ቡና እና የባህርዳር ከተማ ጨዋታ 2-2 ተጠናቋል።

ምሽት ላይ የሳምንቱ ተጠባቂ መርሐ-ግብር በኢትዮጵያ ቡና እና በባህርዳር ከተማ መካከል ሲደረግ ሁለቱም ቡድኖች ባለፈው ሳምንት የቀረቡበትን አሰላለፍ ሳይለውጡ ለጨዋታው ቀርበዋል።


ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ቡናማዎቹ በቁጥር በዝተው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመግባት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ጠንካራ የተከላካይ መስመር ያላቸው የጣና ሞገዶቹ ለቡናማዎቹ የማጥቃት እንቅስቃሴ ፈተና ቢሆኑም በሚቆራረጡ ቅብብሎች ተደራጅተው ከራሳቸው የግብ ክልል ለመውጣት ተቸግረዋል። ሆኖም የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ 5ኛው ደቂቃ ላይ በኢትዮጵያ ቡናዎች አማካኝነት ሲደረግ በፍቃዱ ዓለማየሁ ከሳጥን ውጪ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ መልሶበታል።

የተጠበቀውን ያህል የግብ ዕድሎች ባልተፈጠሩባቸው ቀጣይ ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያልተረጉባቸው ነበሩ። ሆኖም ቡናማዎቹ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር የግብ ዕድል አግኝተው 19ኛው ደቂቃ ላይ በፍቃዱ ዓለማየሁ ያደረገውን ጥሩ ሙከራ መሳይ አገኘሁ እና ያሬድ ባዬህ ተደርበው መልሰውታል።

ከወትሮው በተለየ አስፈሪ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ባጡት ባህርዳሮች በኩል 20ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ታደሠ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ የመጀመሪያው የተሻለ ሙከራቸው ነበር። ሜዳ ላይ በተጫዋቾች መካከል ሲደረጉ የነበሩ  ጉሽሚያዎችም ጨዋታው በተደጋጋሚ እንዲቆም እና የሁለቱም ቡድኖች በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው እንዲቀዛቀዙ ምክንያት ነበር።

ድራማዊ ክስተት በታየባቸው የአጋማሹ የመጨረሻ አምስት ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል ብርቱ ፉክክር ሲደረግባቸው አጋማሹ ሊጠናቀቅ በተጨመሩ 2 ደቂቃዎች ውስጥ ሁለት ግቦች ተቆጥረዋል። በቅድሚያም የጭማሪው የመጀመሪያ ደቂቃ ላይ ብሩክ በየነ ከቅጣት ምት ያሻገረለትን ኳስ ከተከላካዮች ሾልኮ የወጣው ጫላ ተሽታ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮት ቡናማዎቹን መሪ ሲያደርግ ኳሱን ከመሃል ሜዳ የጀመሩት ባህርዳሮች ያንኑ ኳስ በጥቂት ንክኪዎች በማስቆጠር ምላሽ ሰጥተዋል። ግቡንም ፍጹም ጥላሁን ከቀኝ መስመር ከሳጥን አጠገብ ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ቸርነት ጉግሣ አስቆጥሮታል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው እጅግ ተሻሽሎ ሲቀጥል በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በከፍተኛ የጨዋታ ግለት የማጥቃት እንቅስቃሴ ያደረጉት ኢትዮጵያ ቡናዎች 47ኛው ደቂቃ ላይ  ጨዋታውን በድጋሚ መምራት ጀምረዋል። ግቡንም ከቀኝ መስመራቸው የተሻገረውን ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ የነበረው ካኮዛ ዴሪክ ወደ ውስጥ ሲመልሰው ያገኘው ብሩክ በየነ ኳሱ የላይኛውን አንግል ገጭቶ ግብ እንዲሆን አድርጎታል። ግቡ በተቆጠረበት ቅጽበት የባህርዳር ከተማ ተጫዋቾች ኳሱ ከመስመር ወጥቶ ነበር በማለት ከፍተኛ ቅሬታ አሰምተዋል። ቡናማዎቹ በሁለት ደቂቃዎች ልዩነትም ንጹህ የግብ ዕድል ፈጥረው ጫላ ተሺታ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ አባይነህ ፌኖን በፍሬው ሰለሞን ቀይረው በማስገባት መሃል ሜዳው ላይ የተወሰደባቸውን ብልጫ በመጠኑ ለማስመለስ የቻሉት የጣና ሞገዶቹ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር መታተራቸውን ቀጥለው 68ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዋል። ቸርነት ጉግሣ ሀብታሙ ታደሠ ከፍ አድርጎ ያቀበለውን ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ወደ ውስጥ ሲያሻግረው ኳሱን ያገኘው ፍጹም ጥላሁን በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮታል።

ከነበራቸው የጋለ የማጥቃት እንቅስቃሴ በመጠኑ እየተቀዛቀዙ የሄዱት ቡናማዎቹ የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ በመጠኑ መነቃቃት ችለዋል። ለዚህ ማሳያም 73ኛው ደቂቃ ላይ በቀኙ የማጥቃት መስመራቸው ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው ተቀይሮ የገባው መስፍን ታፈሰ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ ሲመልስበት 77ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ተቀይሮ የገባው አማኑኤል አድማሱ ከግራ መስመር በተሻገረለት ኳስ በግንባሩ በመግጨት ግሩም ሙከራ ቢያደርግም የጣና ሞገዶቹ ግብ ጠባቂ ፔፔ ሰይዶ እጅግ ድንቅ በሆነ ቅልጥፍና አግዶበታል። ያንኑ ኳስ ሲመለስ ያገኘው በተመሳሳይ ተቀይሮ የገባው አማኑኤል ዮሐንስም እጅግ ደካማ በሆነ አጨራረስ ወርቃማውን የግብ ዕድል አባክኖታል።


ለተመልካች ማራኪ የሆነ ብርቱ ፉክክር እየተደረገባቸው በቀጠሉት የመጨረሻ ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች እየተፈራረቁ በሚያሳዩት የማጥቃት እንቅስቃሴ አጓጊ የነበሩ ቢሆንም ሁለቱም ቡድኖች ባልተረጋጋ ሂደታቸው የመጨረሻ ኳሳቸውን ውጤታማ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። ሆኖም ግን 95ኛው ደቂቃ ላይ አለልኝ አዘነ ከሀብታሙ ታደሠ በተቀበለው ኳስ ግሩም ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂው በረከት አማረ መልሶበታል ጨዋታውም 2-2 ተጠናቋል።