የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 2-2 ባህርዳር ከተማ

“የሊጉ ሁለት ምርጥ ቡድኖች ፣ ከምርጥ ጨዋታ ጋር ነጥብ የተጋሩበት ጨዋታ እንደመሆኑ ውጤቱ ፍትሃዊ ነው” አሰልጣኝ ኒኮላ ካቫዦቪች

“ጎሎች ያስተናገድንበት መንገድ ያስቆጫሉ” አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው

አሰልጣኝ ኒኮላ ካቫዞቪች – ኢትዮጵያ ቡና

ስለ ጨዋታው …

“በውድድር ዓመቱ ለሊጉ አሸናፊነት ከሚጠበቁት ቡድኖች አንዱ እና በግሌ የሊጉ ምርጡ ቡድን ከሆነው ባህር ዳርን እንደመግጠማችን ከውጤት አንፃር ደስተኞች ነን ፣ ነገር ግን በተቃራኒው ደግሞ የፈጠርናቸውን ዕድሎችን መጠቀም ያለመቻላችን ነገር በጣም ያስቆጫል። ባህር ዳሮች በፈለጉት መልኩ እንዳይጫወቱ ማድረግ ችለናል ነገርግን በጨዋታው ባህር ዳሮች ሦስት ዕድል ብንፈቅድላቸው ሁለቱን ተጠቅመዋል። በእኔ እምነት የሊጉ ሁለት ምርጥ ቡድኖች ከምርጥ ጨዋታ ጋር ነጥብ የተጋሩበት ጨዋታ እንደመሆኑ ውጤቱ ፍትሃዊ ነው።

ሁለቴ መርተው ውጤቱን ማስጠበቅ ስላለመቻላቸው…

“ሰዎች ልብ የማይሉት ነገር ያለ ይመስለኛል ፣ የእኛ ቡድን በታዳጊዎች የተገነባ ነው። በመጀመሪያ ተሰላፊነት ካስጀመርናቸው ተጫዋቾች ውስጥ ሦስቱ ብቻ ናቸው ከ21 ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው ፣ እኛ የሦስት አመት ዕቅድ ይዘን ቡድን ትልቅ ነገር እየገነባን ነው። ተጫዋቾቹ ከዕድሜያቸው አንፃር እጅግ አስገራሚ እንቅስቃሴን እያደረጉ ነው ያሉት ለአብነት ያህል በፍቃዱ ፣ ኤርሚያስ ፣ አማኑኤልን መመልከት እንችላለን። ይህ ቡድን ትልቅ የማደግ አቅም አለው በመሆኑም መሰል ጉድለቶችን በሂደት እየሞላናቸው እንሄዳለን።

ስላገኙት ነጥብ…

“በሜዳው ላይ የተሻልን ነበርን ፣ ከዚህ አንፃር በተመዘገበው ውጤት አላረካንም ፣ ነገርግን በዚህ ወጣት ስብስብ ከሊጉ ምርጥ ቡድን በልጠን መንቀሳቀስ እንደምንችል ለደጋፊያችን ሆነ ለራሳችን ማየት መቻላችን ደስተኛ ያረገናል። ነገርግን በመሻሻላችን መቀጠል ይኖርብናል። ሊጉ ወደ ዕረፍት ከማምራቱ በፊት በቀሩን ሁለት ጨዋታዎች የግድ ማሸነፍ ይኖርብናል።”

አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው – ባህርዳር ከተማ

ከፍተኛ ፉክክር ስለነበረው ጨዋታ …

“ለተመልካች በጣም አዝናኝ የሆነ ነፃ ጨዋታ ነው። በማጥቃት ፣ በመከላከሉ ረገድ የተሻለ ለመስራት ተጫዋቾቻችን ጥረት አድርገዋል። በተደጋጋሚ ወደ ጎል ለመድረስ ያደረግነው ጥረት ውጤታማ ነው ብዬ አስባለሁ። ሆኖም ግን እነርሱ ስድስት ነጥብ ይዘው ነው ከእኛ ጋር ጨዋታቸውን ያደረጉት እኛ ደግሞ ሦስት ነጥብ በጣም ያስፈልገን ነበር ፣ እልህ አስጨራሽ ፉክክር የታየበት ሁኔታ ነው ያለው ጎሎች ያስተናገድንበት መንገድ ያስቆጫሉ ግን እንደ እንቅስቃሴ ተጫዋቾቻችን የነበራቸው የመጫወት ፍላጎት ፣ ጨዋታውን አሸንፎ ለመውጣት ያሳዩት ጥረት እጅግ በጣም የሚያስደስት ነው። ምን አልባት አቻው ያንስብን ይሆናል እንጂ ማሸነፍ ይገባን ነበር ብዬ ነው የማስበው እንደ አጠቃላይ ጥሩ ጨዋታ ነው።”

በመከላከሉ ላይ ስለነበረው መሳሳት…

“ብዙ ሳስቷል ብዬ አላስብም ፣ ጥሩ እየተጫወቱ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው ፣ ግራ ተከላካይ ላይ ወጣት ተጫዋች ነው እየተጠቀምን ያለነው ፤ ከፍራኦል ጉዳት ጋር ተያይዞ። እርሱም ቢሆን በእንደዚህ አይነት ጠንካራ ጨዋታ ውስጥ ያሳየው ፐርፎርማንስ ጠንካራ የሚባል ነው። እንደ ቡድን የመከላከል አደረጃጀታችን ጥሩ ነው የነበረው ረጃጅም ኳሶች ይላኩ ነበር ፣ መልሶ ማጥቃቶች ነበሩ እነዛን የተቆጣጠሩበት መንገድ እጅግ በጣም የሚያስደስት ነው። ምቾት ተሰምቷቸው ነው የተጫወቱት ማለት እችላለሁ። እንደ አጠቃላይ ግን ጨዋታውን በውጤት አጅበን ለመውጣት የነበረን ጥረት እጅግ በጣም አስደሳች ነው። በመጨረሻ ደግሞ የአለልኝ አዘነ ጥረት ወደ ውጤት ተቀይሮ ቢሆን ደግሞ እጅግ ጣፋጭ ይሆን ነበር።

በጨዋታው ፍሬው ሠለሞን እና ቸርነት ጉግሳ ስላስተናገዱት ጉዳት…

“ቶሎ አገግመው ወደ ጨዋታ ይመለሳሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ቀጣይ ጨዋታችን ቅርብ ነው ሐሙስ ነው የምናደርገው ፣ ሁለቱም ለቡድናችን ያስፈልጉናል እንደ አጠቃላይ ግን ሌሎች ተጫዋቾችም ተክተው ሊጫወቱ የሚችሉበት ሁኔታዎች ስለሚኖሩ እንደ ቡድን የተሻለንን ሁሉ እናደርጋለን። በቀጣይም ባሉት ክፍተቶቻችን ላይ የበለጠ ጠንክረን ሰርተን እንመጣለን ብዬ አስባለሁ።”