ሪፖርት | አዳማ ከተማ እና ሀምበርቾ ነጥብ ተጋርተዋል

አራት ግቦች የተቆጠሩበት እና ለተመልካች ሳቢ የነበረው የአዳማ ከተማ እና የሀምበርቾ ጨዋታ 2-2 ተጠናቋል።


በዕለቱ ቀዳሚ መርሐ-ግብር አዳማ ከተማ እና ሀምበር ቾ ሲገናኙ ሁለቱም ቡድኖች ካለፈው የጨዋታ ሳምንታቸው አንፃር የሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ በተመሳሳይ አድርገው ቀርበዋል። አዳማ ከተማ ከወላይታ ድቻው ድላቸው መስዑድ መሐመድ እና አሸናፊ ኤልያስን አሳርፈው ዊሊያም ስለሞንን እና አብዲሳ ጀማልን ሲተኳቸው ሀምበሪቾዎች በቅዱስ ጊዮርጊስ ተረቶ ከነበረው ስብስባቸው ፓሉማ ፖጁን በ ምንታምር መለሰ  ዳግም በቀለን በአቤል ከበደ ቀይረው በማስገባት ለጨዋታው ቀርበዋል።

ቀን 9 ሰዓት ላይ በዋና ዳኛው ሀብታሙ መንግሥቴ ፊሽካ በተጀመረው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ የመጀመሪያ 30 ደቂቃዎች ለተመልካች ማራኪ የሆነ ፉክክር ተደርጎባቸዋል። ጨዋታው ግብ የተቆጠረበት ገና በ 6ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ዊልያም ሰለሞን በግሩም ዕይታ ሰንጥቆ ያቀበለውን ኳስ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ይዞት የገባው ጀሚል ያዕቆብ ወደ ውስጥ የቀነሰውን ኳስ ያገኘው አብዲሳ ጀማል በቀላሉ በማስቆጠር አዳማ ከተማን መሪ አድርጓል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በተለይም በቀኙ የማጥቂያ መስመራቸው የአቻነት ግብ ፍለጋ ሲታትሩ የነበሩት ሀምበሪቾዎች 12ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። ዳግም በቀለ ከቀኝ መስመር ከሳጥን አጠገብ ያሻገረለትን ኳስ አማካዩ በፍቃዱ አስረሳኸኝ በጥሩ አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

በሁለቱም በኩል ክፍት በነበረው ጨዋታ አዳማዎች ከራሳቸው የግብ ክልል ኳስ መስርተው ለመውጣት ሲሞክሩ ሀምበሪቾዎች በአንጻሩ የሚያገኙትን ኳስ በፍጥነት የተጋጣሚ የግብ ክልል በማድረስ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። ሆኖም ቀዝቃዛ በነበሩት የአጋማሹ የመጨረሻ 15 ደቂቃዎች በአዳማ ከተማ በኩል 35ኛው ደቂቃ ላይ ዊልያም ሰለሞን በሳጥኑ የግራ ክፍል ይዞት ገብቶ ያደረገውን ሙከራ የኳሱ ኃይል የለሽነት ተጨምሮበት ግብ ጠባቂው ፖሉማ ፖጁን ሲያስወጣበት በሀምበሪቾዎች በኩል 43ኛው ደቂቃ ላይ አፍቅሮት ሰለሞን በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ይዞት በገባው ኳስ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ሰኢድ ሀብታሙ በቀላሉ ይዞበታል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በተመሳሳይ ሂደት በመጠነኛ ፉክክር ሲቀጥል በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ለማሸነፍ በነበራቸው ግለት ኳሶችን በተደጋጋሚ ወደ ሳጥን ለማድረስ ጥረት ቢያደርጉም የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ተቸግረዋል። ሆኖም በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ የተወሰደባቸው ሀምበሪቾዎች 62ኛው ደቂቃ ላይ በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ግብ አስቆጥረው ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። በረከት ወንድሙ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ ሲመልስበት ኳሱን ያገኘው ዳግም በቀለ በተረጋጋ አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

አዳማዎች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ዮሴፍ ታረቀኝ እና ቦና ዓሊን ቀይረው በማስገባት የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ላይ ነፍስ ዘርተውበታል። በዚህ ጠንካራ እንቅስቃሴያቸውም 77ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያው ግባቸውን ባስቆጠሩበት ፍጹም ተመሳሳይ ሂደት የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። ዊልያም ሰለሞን በድንቅ ዕይታ ሰንጥቆ ያቀበለውን ኳስ ጀሚል ያዕቆብ በቀኙ የሳጥኑ ክፍል ሮጦ በመግባት ለዮሴፍ ታረቀኝ ሲቀንሰው ኳሱን ያገኘው ተቀይሮ የገባው ዮሴፍም በግሩም የተረጋጋ አጨራረስ ግብ  አድርጎታል።

በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች ሀምበሪቾዎች የሊጉን የመጀመሪያ ነጥባቸውን ለማግኘት በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ መሻሻል በማሳየት ጨዋታውን ለማረጋጋት ጥረት ሲያደርጉ በተሻለ የጨዋታ ስሜት የነበሩት አዳማዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር መታተራቸውን ቀጥለው ታይተዋል። በዚሁ ግለታቸውም 91ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው ነበር። ተቀይሮ የገባው አሸናፊ ኤያልስ ከ ሀይደር ሸረፋ በተቀበለው ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ጠርዝ ላይ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፖሉማ ፖጁን አግዶበታል። ይህም የጨዋታው የተሻለ የመጨረሻ ሙከራ ሆኖ ጨዋታው 2-2 ተጠናቋል።