ሲዳማ ቡና ከዚህ በኋላ የአጥቂውን ግልጋሎት አያገኝም

ባሳለፍነው ዓመት ሲዳማ ቡናን የተቀላቀለው ጋናዊው አጥቂ ክለቡን እንደማያገለግል ታውቋል።

የዓምናው የውድድድር አጋማሽ ላይ ሲዳማ ቡናን በመቀላቀል ቡድኑ በሊጉ ለመቆየት ወሳኝ ሚና ከነበራቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ የነበረው ጋናዊው አጥቂ ፊሊፕ አጃህ በህመም ምክንያት ቡድኑን እንደማያገለግል ተሰምቷል።

ሲዳማ ቡና በመጀመርያው ሳምንት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በነበረው ጨዋታ ጉልበቱ ላይ ጉዳት አስተናግዶ ከወጣ በኋላ ወደ ሜዳ ያልተመለሰው እና ከክለቡ ጋር እስከ ውድድሩ አጋማሽ ውል የነበረው ፊሊፕ አጃህ የህመሙ ሁኔታ መሻሻል ባለማሳሳየቱ ወደ ሀገሩ ሊያቀና መሆኑን አውቀናል።

ይህን ተከትሎ ሲዳማ ቡና በቀጣይ ባሉበት የሊጉ ስምንት ጨዋታዎች የአጥቂውን የመጨረሻ የውል ጊዜያት ግልጋሎት እንደማያገኝ ታውቋል። በተያያዘ ዜና ሌላኛው በዚህ ዓመት ቡድኑን የተቀላቀለው አጥቂ አብዱራህማን ሙባረክ እስካሁን በህመም ቡድኑን እያገለገለ እንደማይገኝ ሲታወቅ በቀጣይ ሳምንታት ግን ወደ ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ተነግሯል።