መረጃዎች| 26ኛ የጨዋታ ቀን

በሰባተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ የሚደረጉትን ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።  

መቻል ከ አዳማ ከተማ   

ሁለት በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኙ ቡድኖችን የሚያገናኘውን ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ ፍልሚያ ይሆናል።

በባህር ዳር ከተማዎች ሽንፈት ካስተናገዱ በኋላ ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ሦስት ድልና አንድ የአቻ ውጤት ያስመዘገቡት መቻሎች አስራ ሦስት ነጥቦች ሰብስበዋል። መቻሎች በውጤት ረገድ ጥሩ የውድድር ዓመት እያሳለፉ ቢገኙም በእንቅስቃሴ ረገድ ግን መሻሻል ይጠበቅባቸዋል። በተለይም ቡድኑ በአማካይ ክፍል ያለው ድክመት ጨዋታ እንዳይቆጣጠሩና የግብ ዕድሎች እንዳይፈጥሩ እክል ሆኖባቸዋል። ይህ ችግር ባለፉት ጨዋታዎች በጉልህ የታየ ሲሆን በጉዳት የነበሩት ተጫዋቾች ከጉዳት መመለሳቸው ተከትሎ ለውጦች ሊኖር እንደሚችልም ይገመታል። በተለይም የከነዓን ፣ ሽመልስ እና በረከት መመለስ የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ይለውጣል ተብሎ ይገመታል። መቻሎች ተቸግረውም ቢሆን ተከታታይ ድሎች ማስመዝገባቸው የቡድኑ የስነ-ልቦና ከፍታን ያሳያል። ከዚህ በተጨማሪ በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ምንም ግብ ያላስተናገደው የተከላካይ ክፍል የቡድኑ ጠንካራ ጎን ነው። በነገው እለት በተከታታይ አራት ጨዋታዎች ሁለት ሁለት ግቦች ያስቆጠረው የአዳማ ከተማ የአጥቂ ክፍል እና በሦስት ጨዋታዎች ምንም ግብ ያላስተናገደው የመቻል የተከላካይ ክፍል የሚያደርጉት ፍጥጫም የጨዋታው ትኩረት ሳቢ ጉዳይ ነው።

ከተከታታይ ሁለት የአቻ ውጤቶች በኋላ በተከታታይ ጨዋታዎች ድል አስመዝግበው ነጥባቸውን ወደ አስራ ሁለት ከፍ ያደረጉት አዳማ ከተማዎች በውድድር ዓመቱ ሽንፈት አልገጠማቸውም። አዳማ ከተማዎች በአራት ተከታታይ ጨዋታዎች በአማካይ በጨዋታ ሁለት ግቦች ያስቆጠረ ጠንካራ የማጥቃት አጨዋወት አላቸው። የአማካይ ክፍሉም ቢሆን በመጨረሻው ኢትዮጵያ ቡናን ባሸነፉበት ጨዋታ መጠነኛ መቀዛቀዝ ብያሳይም ሌላው የቡድኑ ጥንካሬ ነው። አዳማዎች በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ግባቸውን ሳያስደፍሩ የወጡበት አጋጣሚ የለም። በመጀመርያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች የቡድኑ ዋነኛ ጥንካሬ የነበረው ክፍልም ጥንካሬውን ማስቀጠል ተስኖታል። ቡናን ባሸነፉበት ጨዋታም ለስህተቶች ተጋላጭ ሲሆን ታይቷል። አሰልጣኙም የቡድኑ ሚዛን ላይ ማስተካከያ ማድረግና የስህተቶቹን መጠን እንዲቀንስ የሚያስችል መጠነኛ ጥገና የማድረግ ሥራ ይጠብቀዋል።

መቻሎች ባለፈው ጨዋታ በቀይ ከሜዳ የወጣው ግሩም ሐጎስ በቅጣት አያሰልፉም ፤ ጉዳት ላይ የነበሩት ከነዓን ማርክነህ ፣ ሽመልስ በቀለ እና በረከት ደስታ ግን ከጉዳት አገግመው ለጨዋታ ዝግጁ ሆነዋል። ፍፁም ዓለሙም በጥሩ የጤንነት ሁኔታ ይገኛል፤ በቅርቡ ወደ ጨዋታ ይመለሳል ተብሎም ይጠበቃል። በአዳማ ከተማ በኩል አድናን ረሻድ እና ቦና ዓሊ በጉዳት እንዲሁም አብዲሳ ጀማል እና ዊልያን ሰለሞን በዲሲፕሊን ምክንያት የነገው ጨዋታ የሚያመልጣቸው ይሆናል።

መቻል እና አዳማ በሊጉ ታሪክ ነገ 32ኛ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። እስካሁን 13 ጊዜ ነጥብ ሲጋሩ አዳማ 10 መቻል ደግሞ 8 ድሎችን አሳክተዋል። በጨዋታዎቹ ከተቆጠሩ 49 ግቦች ውስጥ አዳማ 27 መቻል ደግሞ 22 ግቦችን አስመዝግበዋል።

ጨዋታውን ሔኖክ አበበ በዋና ዳኝነት ይመራዋል። ኢንተርናከል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው ከአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ መልስ ከሙሉነህ በዳዳ ጋር በረዳት ዳኝነት ሲሰየም ፣ ሌላኛው በያዝነው ሳምንት በተመሳሳይ የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ ጨዋታን የመራው ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ አራተኛ ዳኛ ሆኖ ተመድቧል።

ባህር ዳር ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ

በሁለት ነጥብ የሚበላለጡ ቡድኖችን የሚያገናኘው ጨዋታ ምሽት 12:00 ላይ ይከናወናል።

ባለፈው ሳምንት የሊጉን መሪ አሸንፈው ነጥባቸውን ወደ አስራ አንድ ከፍ ያደረጉት ባህር ዳሮች ወደ ሊጉ አናት ለመጠጋት ሀዋሳ ከተማን ይገጥማሉ። የጣና ሞገዶቹ በአንደኛው ሳምንት በመድን ከደረሰባቸው የሦስት ለሁለት ሽንፈት በኋላ ሽንፈት አልባ ጉዞ ቢያደርጉም የወጥነት ችግር ይታይባቸዋል፤ እስካሁን ድረስም ተከታታይ ድል ማስመዝገብ አልቻሉም። ሆኖም ጨዋታዎቹ በሊጉ አናት ላይ ከሚገኙ ክለቦች ጋር እንደመሆኑ ከመርሀ-ግብሮቹ ክብደት አንፃር መጥፎ የሚባል ውጤት አይደለም።
በነገው ዕለት ሀዋሳ ከተማን የሚያሸንፉ ከሆነም ለመጀመርያ ጊዜ የተመዘገበ ተከታታይ ድል ይሆናል። የጣና ሞገዶቹ የተከላካይ ክፍል በመጀመርያዎቹ ሦስት ጨዋታዎች በአማካይ ሁለት ግቦች አስተናግዶ ነበር። ከዛ በኋላ ባደረጓቸው ጨዋታዎች ግን ይበልጥ ተሻሽሎ በሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ነው ያስተናገደው። ይህም በቡድኑ ውስጥ ከታዩት ጉልህ መሻሻሎች አንዱ ነው። ሌላው መሻሻል ያሳየው የጣና ሞገዶቹ ክፍል አማካይ ጥምረቱ ነው፤ በተለይም አባይነህ ፊኖ እያሳየው ያለው ብቃት በጥሩነት የሚነሳ ነው። በነገው ዕለትም እነዚህን ጥንካሬዎች ማስቀጠል ይጠበቅባቸዋል። ለምን ቢባል የነገው ተጋጣሚያቸው ጠጣር ከሚባሉ ክለቦች አንዱ የሆነውን ሀዋሳ ከተማ ነው።

ባለፈው ሳምንት ከተከታታይ የአቻ እና የድል ውጤቶች በኋላ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያው ሽንፈታቸው የቀመሱት ሀዋሳ ከተማዎች ወደ ድል ለመመለስ ከባህር ዳር ከተማን ጋር ይገጥማሉ። ሀዋሳዎች ሽንፈት በገጠማቸው ጨዋታ ላይ ከሌላው ጊዜ በተለየ ተዳክመው ታይተዋል። በዋነኝነት በተከላካይ ክፍሉ የነበረው ክፍተትም በጉልህ የሚጠቀስ ድክመት ነበር። ቡድኑ ከዚህ ቀደም ለተከታታይ አራት ጨዋታዎች ምንም ግብ ያላስተናገደ ንቁና ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ነበረው። በንግድ ባንክ በተሸነፉበት ጨዋታ ላይ ግን የተጋጣሚን ጥቃት በንቃት የመመከት ድክመት ታይቶባቸዋል። አሰልጣኙም ይህንን ችግር የመቅረፍና የተከላካይ ክፍሉ ወደ ቀድሞ ጥንካሬው የመመለስ ስራ ይጠብቃቸዋል። በነገው ዕለትም ጠንካራ የማጥቃት ክፍል ያለው ቡድን ስለሚገጥሙ የተከላካይ ክፍሉ ጥንካሬ መመለስ ወሳኝ ነው። ባህር ዳር ከተማዎች ባለፈው ሳምንት ሀዋሳን ካሸነፈው ንግድ ባንክ ጋር የሚመሳሰል የማጥቃት አጨዋወት ያለው ቡድን ስለሆነም ቡድኑ የመጨረሻው ጨዋታ ስህተቶቹን አርሞ መግባት ግድ ይለዋል። ሌላው በኃይቆቹ ሊነሳ የሚገባው ክፍተት የቡድኑ የቆየ የማጥቃት አጨዋወት ድክመት ነው። ቡድኑ ከፋሲል ከነማ ጋር ሦስት ለሦስት አቻ ከተለያየበት ጨዋታ በኋላ ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ማስቆጠር የቻለው የግብ መጠን ሁለት ብቻ ነው። ይህ ቁጥርም የሀዋሳ የማጥቃት አጨዋወት ምን ያህል ለውጥ እንደሚያስፈልገው ማሳያ ነው። ቡድኑ ወደ ሁለቱ አጥቂዎች በሚሻገሩ ኳሶች የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ሲያደርግ ቢታይም የማጥቃት አጨዋወቱ ውጤታማነት ግን ደረት አያስነፋም ነው።

ባህር ዳር ከተማዎች በጉዳት ወይም በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም፤ በሀዋሳዎች በኩል ግን ባለፈው ጨዋታ ጉዳት ያስተናገደው እዮብ አለማየሁ የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው።

ባህር ዳር እና ሀዋሳ በሊጉ እስካሁን በ8 ጨዋታዎች የተገናኙ ሲሆን ዕኩል ሰባት ሰባት ጎሎችን አስቆጥረዋል። ሦስት ጊዜ ነጥብ ከመጋራታቸው ባሻገር ሀዋሳ ከተማ 3 ባህር ዳር ከተማ ደግሞ 2 ድሎችን አሳክተዋል።

ጨዋታውን ዳንኤል ይታገሱ በዋና ዳኝነት ይመራዋል፤ ሻረው ጌታቸው እና መሐመድ ሁሴን በረዳት ዳኝነት፤ አዳነ ወርቁ በበኩሉ አራተኛ ዳኛ በመሆን ተሰይሟል።