የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | የ4ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ

የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የአራተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታ ሦስት ጨዋታዎች ተደርገው ቦሌ ክ/ከተማ ብቸኛው የዕለቱ ባለድል ሆኗል።

ከተጀመረ አራተኛ ሳምንቱን በያዘው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ አራት ጨዋታዎች ተደርጎ ሁለቱ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ የቀርው አንድ ጨዋታ በመሸናነፍ ተጠናቋል።

ረፋድ አራት ሰዓት ላይ ንግድ ባንክን ከሲዳማ ቡና ያገናኘው ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል። ብዙ የግብ ሙከራዎችን ያደረጉት ንግድ ባንኮች ጠንካራ ሆኖ የዋለውን የሲዳማ ቡናን ተከላካይ መስመር አልፎ ግብ ማስቆጠር ተስኗቸዋል። በሁለቱም አጋማሽ ጠንከር ያሉ ኳሶችን ሲሞክሩ የተሰተዋሉት ንግድ ባንኮች ገና በአንደኛው አጋማሽ የተጫዋች ቅያሪ አድርገው ኳሱን ተቆጣጥሮ በመጫወት ጥሩ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ግብ ሲያስቆጥሩ ወተዋል። ሲዳማ ቡና በአንፃሩ ጥሩ የመከላከል ስልት ይዞ የገቡ ሲሆን በመልሶ ማጥቃት ግቢ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል።

ከሰዓት ስምንት ሰዓት ላይ በተደረገው መርሃ ግብር ቦሌ ክ/ከተማ ከ ይርጋጨፌ ቡና ተገናኝተው በቦሌ 2ለ1 አሸናፊነት የተጠናቀቀው ጨዋታ የዕለቱ በመሸናነፍ የተጠናቀቀ ጨዋታ ሆኖ ተመዝግቧል።

የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ የጨዋታ በላይነት የወሰዱት ቦሌ ክ/ከተማዎች በተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተስተውለዋል። በ30ኛው ደቂቃ የቦሌዋ የፊት መስመር ተጫዋች የሆነችው ትዕግሥት ወርቄ ኳሱን እየገፋች የይርጋጨፌ ግቢ ክልል በመትገባበት ሰዓት በተሰራባት ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት አስገኝታ ፍቅርአዲሰሰ ገዛኸኝ ወደግበነት ቀይራ መሪ መሆን ችለዋል።

ይርጋጨፌ የአቻነት ግብ ፍለጋ አንድ ላይ በመሆን ወደ ተቃራኒ ቡድን በመሄዱበት ወቅት የቦሌ ተከላካዮች ኳስን አስጥሎ በመልሶ ማጥቃት በትዕግሥት ወርቄ አማካኝነት ሁለተኛ ግብ በማስቆጠር 2ለ0 መምራት ችለዋል። ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በተደጋጋሚ ግብ ለማስቆጠር ሙከራ ሲያደርጉ የተሰተዋሉት ይርጋጨፌ ቡናዎች በ42ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ በግንባር ገጭታ አስቆጥራ 2-1 እንዲመሩ አስችላለች።

በሁለተኛው አጋማሽም ብዙ የግብ ሙከራዎች በታዩበት በዚህ ጨዋታ በይርጋጨፌ ቡና በኩል ብዙ የሚያስቆጩ ኳሶችን ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። የመጀመሪያ አጋማሽ ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ቀርተው እያለ ያገኙት ፍፁም ቅጣት ምት ትርሲት አምክናለች። እንዲሁ ቦሌዎችም ሌላ ግብ ለማስቆጠር ሙከራዎች ለማድረግ ሲጥሩ ተመልክተናል።

የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ በሆነው በ10:00 ሰዓቱ ጨዋታ ብዙ የግብ ሙከራዎች ባልታየበት መርሃ ግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና መቻል ነጥብ ተጋርተዋል።

ሁለቱም ቡድኖች የመካለከል ባህርይ ባሳዩት በዚህ ጨዋታ እምብዛም የግብ ሙከራዎች ያልታዩ ሲሆን ጨዋታው ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩት ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጫና ፈጥሮ በመጫወት የግብ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተመልክተናል። መቻሎችም በበኩላቸው ኳስን ለመቆጣጠር ጥረት አድርገዋል።የመቻሏ መሰረት ወርቅነህ ባለቀ ደቂቃ ጥሩ ኳስ አግንታ ሳትጠቀም የቀረችው አጋጣሚ ምናልባትም አሸነፈው መውጣት የሚችሉበት አጋጣሚ መሆን ይችል የነበረ ቢሆንም ሳይጠቀሙ ቀርተው ነጥብ ተጋርተዋል።