መረጃዎች | 26ኛ የጨዋታ ቀን

ሰባተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ነገም ሲቀጥሉ የሸገር ደርቢ ላልተወሰነ ጊዜ ቢራዘምም ቀሪውን አንድ ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎችን አዘጋጅተናል።

ሁለት ተከታታይ የአቻና የሽንፈት ውጤቶች ያስመዘገቡ ቡድኖች የሚያገናኘውን የሆሳዕና እና የመድን ጨዋታ ነገ በተያዘለት ቀደም ያለ ሰዓት (12:00) እንደሚከናወን ይጠበቃል።

በስድስት ሳምንታት ውስጥ ሁለት ሽንፈትና አራት የአቻ ውጤቶች በማስመዝገብ ከ ድል ጋር መታረቅ ያልቻሉት ሀድያ ሆሳዕናዎች የአሰልጣኝ ቅያሪ ካደረጉ በኋላም ተከታታይ የአቻ ውጤቱን መቀየር አልቻሉም። በነገው ጨዋታም ይህንን መጥፎ ክብረ ወሰን ለመቀየር በተመሳሳይ ሁኔታ ያለውን ኢትዮጵያ መድን ይገጥማሉ። ሆሳዕናዎች በተከታታይ አራት ጨዋታዎች ምንም ግብ ማስቆጠር ያልቻለ ደካማ የማጥቃት አጨዋወት አላቸው፤ ሆኖም ከሲዳማ ቡና ጋር አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ላይ ከሌላው ጊዜ በተሻለ ጥሩ ተንቀሳቅሰዋል። በጨዋታው ግብ ማስቆጠር ባይችሉም የፈጠሯቸው ዕድሎች ግን ተጋጣሚያቸውን ፈተና ውስጥ የከተቱ ነበሩ። ቡድኑ በአጥቂ ክፍሉ ላይ ያሳየው ውስን መሻሻልም በበጎ ጎኑ ይነሳለታል። ሌላው የሀድያ ሆሳዕና ጠንካራ ጎን የተከላካይ ክፍሉ ጥንካሬ ነው በተከታታይ አራት ጨዋታዎች ላይም መረቡን አላስደፈረም። አሰልጣኙ የመጀመርያው ድል ለማስመዝገብ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ምንም ግብ ሳይቆጠርበትና ሳያስቆጥር የወጣው አጨዋወት ላይ ውስን ለውጥ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ወደ መከላከሉ ያደላ የቡድኑ የአጨዋወት ሚዛን ማስተካከካያ እንደሚያስፈልገው ቁጥሮችም ምስክር ናቸው።

ኢትዮጵያ መድኖች ከተከታታይ ሁለት ሽንፈት ለመላቀቅና ወደ ወራጅ ቀጠና የተንሸራተተው ነጥባቸውን ከፍ ለማድረግ የግድ ሦስት ነጥብ ያስፈልጋቸዋል። መድኖች ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ምንም ድል ማስመዝገብ አልቻሉም፤ ማግኘት ከሚገባቸው አስራ አምስት ነጥቦች ማሳካት የቻሉት ሁለቱን ብቻ ነው። ይህም የቡድኑ መጥፎ ወቅታዊ አቋም አንዱ ማሳያ ነው። በተለይም ኳስና መረብ ማገናኘት የተሳነው የማጥቃት ጥምረት የቡድኑ ዋነኛ ድክመት ተደርጎ ይወሰዳል። ቡድኑ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ምንም ግብ አላስቆጠረም። አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ይህንን ችግር ለመቅረፍ
የግብ ዕድሎች መፍጠር የተሳነው የአማካይ ክፍላቸው ላይ ከምያደርጉት ለውጥ በዘለለ የሚገኙትን ጥቂት ዕድሎች ወደ ግብነት መቀየር የተሳነው የአጥቂ ጥምረትም ለውጥ እንደሚያስፈልገው ባለፉት ጨዋታዎች ታይቷል። ቡድኑ በመቻል በተሸነፈበት ጨዋታ ላይ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ብልጫ ቢወስድም የተፈጠሩ ዕድሎች ጥራትና ብዛት ካየን ግን ጥቂት ናቸው። በመድን በኩል ሀቢብ ከማል እና አዲስ ተስፋዬ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው።

አምና ሁለቱ ቡድኖች በተገናኙባቸው ጨዋታዎች በመጀመሪያው ዙር ኢትዮጵያ መድን 1-0 ሲያሸንፍ በሁለተኛው ዙር ሀዲያ ሆሳዕና 2-0 ረቷል።

ጨዋታው በባህሩ ተካ መሐል ዳኝነት ይመራል፤ ደረጄ አመራ እና አብዱ ዓሊ ረዳቶች፤ ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ በበኩሉ በአራተኛ ዳኝነት ተመድቧል።