የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ | መሪው ቦሌ ነጥብ ጥሏል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 5ኛ ሣምንት የመጨረሻ ቀን አራት ጨዋታዎች ተደርገው ሶስቱ ጨዋታዎች በአቻ ሲጠናቀቁ ሲዳማ ቡና የዕለቱ ብቸኛ ባለ ድል በመሆን የዓመቱን የመጀመሪያ ሦስት ነጥብ አስመዘገቧል።

የቀኑ የመጀመሪያ ጨዋታ በሆነው መርሐግብር ሀምበርቾ እና አርባምንጭ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል። በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ የበላይነት በመውሰድ ኳስን ተቆጣጥሮ የተጫወቱት ሀምበርቾዎች በተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን አድርገዋል።

አርባምንጭ ከተማዎች በአንጻሩ በመጀመሪያው አጋማሽ ደካማ እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን 33ኛው ደቂቃ ላይ የሀምበርቾ ከተማዋ የፊት መስመር ተጫዋች ፍሬነሽ ዩሐንስ ከሳጥን ውጪ ባስቆጠረችው ግብ በሀምበርቾ መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት ያደረጉት አዞዎቹ የአቻነት ግብ ፍለጋ በርካታ የግብ ሙከራዎችን አድርገዋል። ወደ ተቀራኒ ቡድን ኳስን እየገፉ በሚሄዱበት አጋጣሚ በአጥቂያቸው በፎዚያ መሐመድ ላይ ጥፋት ተሠርቶ የተሰጠውን ቅጣት ምት ሰርካለም ባሣ ቀጥታ ወደ ግብ በመምታት ኳስና መረብን አገናኝታ አርባምንጭ ከተማዎች አቻ እንዲሆኑ አድርጋለች።

የአቻነት ግብ ካስቆጠሩ በኋላ የጨዋታ በላይነትን የወሰዱት አዞዎቹ ተጨማሪ ግብ ፍለጋ ተጭነው ሲጫወቱ ተስተውለዋል። ሆኖም ግን ጨዋታው 1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ሲዳማ ቡና በሰፊ የግብ ልዩነት ቅዱስ ጊዮርጊስን በማሸነፍ የዓመቱን የመጀመሪያ ድሉን አስመዝግቧል። ከመጀመሪያው አጋማሽ ጀምሮ ፍፁም የጨዋታ በላይነት የወሰዱት ሲዳማ ቡናዎች በማህሌት ምትኩ ፣ በባዮሽ ኪንባ ፣ በቤዛዊት ንጉሤ እና በሰናይት ኡራጎ አራት ግቦች ፈረረኞቹን 4ለ0 ረተዋል።

በውድድር ዘመኑ ምንም ድል ያላስመዘገው  ሲዳማ ቡና ውጤት ፍለጋ የግብ ሙከራዎችን ገና ጨዋታው እንደጀመረ ነበር ማድረግ የጀመረው። ከብዙ አስቆጪ የግብ ሙከራዎች በኋላ በቅብብሎሽ ወደ ተቃራኒ ግብ ክልል በገቡበት ቅፅበት በማህሌት ምትኩ ላይ ጥፋት ተሠርቶ ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ራሷ ማህሌት ምትኩ በ28ኛው ደቂቃ ወደ ግብነት ቀይራው ዕረፍት 1ለ0 እየመሩ ወጥተዋል።

በሁለኛው አጋማሽ ጠንከር ብለው ተጨማሪ ግብ ፍለጋ የገቡት ሲዳማ ቡናዎች ሁለተኛው አጋማሽ አንደተጀመረ አከታትለው ባስቆጠሯቸው ግቦች መሪነታቸውን ሲያጠናክሩ በ47ኛው ደቂቃ ባዩሽ ኪንባ ከመሃል ሜዳ አከባቢ የቆመ ኳስ ወድግብ አነጣጥራ በመምታት ግብ አስቆጥራ 2ለ0 እንዲመሩ አስችላለች። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነትም የቅዱስ ጊዮርጊስን ተከላካይ መስመር አዘናግታ ኳስ ገፍታ በመግባት ቤዛዊት ንጉሤ 3ኛውን ግብ አስቆጥራለች።

ዛሬ ተዳክመው የገቡት ፈረሠኞቹ የግብ ሙከራዎችን ሲያደረጉ አልተስተዋሉም። በተቃራኒው ሲዳማ ቡና ተሽሎ በመገኘት በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችሏል።

80ኛው ደቂቃ ላይም በእርስ በርስ ቅብብሎሽ የሲዳማ ቡናዋ ሰናይት ኡራጎ አራተኛ ግብ አስቆጥራ በግብ ተንበሽብሸው 4ለ0 በሆነ ውጤት የመጀመሪያ ድላቸውን አሳክተዋል።

ከቀኑ 8:00 ሰዓት ላይ በተደረገው በሌላኛው መርሐግብር አዲስ አበባ ከተማ እና አዳማ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል። በመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም በቡድኖች መካከል ደካማ እንቅሰቃሴ የተስተዋለ ሲሆን የግብ ሙከራዎችን አላስመለከቱንም።

በሁለኛው አጋማሽ የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ሁለቱም ቡድኖች ተሻሽለው ሲቀርቡ ከአንደኛው አጋማሽ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ያደረጉት አዳማ ከተማዎች በ51ኛው ደቂቃ በፊት መስመር ተጫዋቻቸው በሄለን እሸቱ አማካኝነት ከርቀት በተቆጠረ ግብ መሪ መሆን ችለዋል።

ተመጣጣኝ በነበረው በዚህ ጨዋታ ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የአቻነት ግብ ፍለጋ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የተስተዋሉት አዲስ አበባ ከተማዎች ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ በምትታወቀው በአጥቂያቸው በቤተልሄም መንተሎ አማካኝነት 68ኛው ደቂቃ ላይ አቻ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል።

አንድ ዕኩል ከሆኑ በኋላ በአዳማ ከተማ በኩል የመከላከል ባሕርይ የታየ ሲሆን አዲስ አበባ ከተማዎች በአንፃሩ የግብ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተው ጨዋታው 1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

የሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር የሆነው በሀዋሳ ከተማ እና በቦሌ ክ/ከተማ መካከል የተደረገው ጨዋታ በአንደኛው አጋማሽ በቁጥር ብዙ የሆኑ የግብ ሙከራዎች ያስመለከተ ጨዋታ ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙ የግብ ሙከራዎች ቢደረጉም ያለ ግብ 0ለ0 ወደ መልበሻ ክፍል ገብተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ጥሩ እንቅሰቃሴ ማድረግ የቻለው ሀዋሳ ከተማ ተቀይራ በገባችው በረድዔት አስረሳኝ አማካኝነት ለግብ የተቃረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል።

ቦሌ ክ/ከተማ በአንጻሩ የሊጉ መሪነታቸውን ለማስቀጠል አንድ ነጥብ በቂያቸው የነበረ በመሆኑ ጨዋታውን በመከላከል ሲጫዎቱ ተስተውለዋል።

ካሸነፉ የሊጉ መሪ ስለሚሆኑ ብዙ ጫና በማሳደር በተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች አስቆጪ ሙከራዎችን በአጥቂዎቻቸው አማካኝነት አድርገዋል። መደበኛው የጨዋታው ክፍለ ግዜ ተጠናቆ ሽርፍራፊ ደቂቃዎች ሲቀሩም ከመስመር ረዲዔት አስረሳኸኝ ያሻገረችውን ኳስ ቱሪስት ለማ ሳትጠቀምበት ቀርታ ጨዋታው 0ለ0 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።