ከፍተኛ ሊግ | ኤሌክትሪክ የመጀመርያ ሽንፈት ሲያስተናግድ ነገሌ አርሲ መሪነቱን አጠናክሯል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ የስድስተኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እና ሀዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ ቀጥለው ነገሌ አርሲ፣ ንብ እና ወልዲያ ድል አስመዝግበዋል።

ምድብ ሀ

የእለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከንብ አገናኝቶ ንብ 1-0 በማሸነፍ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ተከታታይ የድል ጉዞን ገቷል። በጨዋታው ኤሌክትሪክ በቅብብል ወደ ግብ በመድረስ አደጋ ለመፍጠር ጥረት ሲያረጉ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ይዞ የገባው ንብ ኳስን በፈጣን ቅብብል ተደጋጋሚ ኳስን በመስመር በኩል ጫና በመፍጠር ግብ ለማስቆጠር ጥረት አርገዋል። በ36ኛው ደቂቃ የንብ ተጫዋች የሆነው ናትናኤል ሰለሞን ከግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ያባከነው ኳስም በአጋማሹ የተፈጠረ መልካም የጎል እድል ነበር።

ከእረፍት መልስ ኤሌክትሪክ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ጫና ፈጥሮ ሲጫወት ንብም በጥንቃቄ በመጫወት እና በረጃጅም ኳስ ወደ ግብ በመቅረብ በመጨረሻ ደቂቃ የማሸነፍያ ጎል አግኝቷል። በዚህም በ89ኛው ደቂቃ ከንብ በኩል ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ናትናኤል ሰለሞን ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ ወደ ግብ ቀይሮ በንብ አሸናፊነት ጨዋታው ተጠናቋል። ውጤቱ ተከታታይ አምስት ጨዋታዎችን ያሸነፈው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የመጀመርያ ሽንፈቱን ያስተናገደበት ሆኗል።

የእለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ጅማ አባቡና እና ኮልፌ ቀራኒዮን አገናኝቶ ያለ ጎል ተጠናቋል። ጅማ አባቡና በኳስ ቁጥጥር ኮልፌ ቀራኒዮ ደግሞ በመከላከልና በመልሶ ማጥቃት የተሻሉ ሆነው ታይተዋል። ጨዋታው መጀመሪያ አከባቢ የጅማ አባ ቡናው ተጫዋች ጴጥሮስ ገዛኸኝ በግልፅ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ማስቆጠር ተስኖት ጥፋት ተሰርቶብኛል ብሎ ቢወድቅም የመሀል ዳኛ ጨዋታው እንዲቀጥል አድርጓል።

ከእረፍት መልስ ጅማ አባቡና የተጫዋች ቅያሬ በማድረግ ጥሩ እንቅስቃሴ ለማድረግ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። የፈጠሯቸው ጥሩ ጥሩ እድሎችንም የኮልፌ ቀራኒዮ ግብ ጠባቂ አዲስ ኪዳን አምክኗል። ጨዋታውም ምንም ግብ ሳይቆጠርበት ተጠናቋል።

የእለቱ ሦስተኛ ጨዋታ ሀላባ ከተማን ከሞጆ ከተማ አገናኝቶ ጥሩ የጨዋታ ፍሰት ቢስተዋልበትም እንደቀደመው ጨዋታ ሁሉ ያለ ጎል ተጠናቋል። በመጀመራው አጋማሽ በ34ኛው ደቂቃ የሀላባ ከተማው ሳሙኤል ተስፋዬ ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ የግቡን ቋሚ ገጭቶ ግብ ከመሆን የቀረው ኳስ ፣ ከእረፍት መልስ በ65ኛው ደቂቃ የሞጆ ከተማው የፊት መስመር ተጫዋች ጉራቦ ሀሰን አስገራሚ ሙከራ የሞከረ ቢሆንም የሀላባ ከተማ ግብ ጠባቂ በግሩም ሁኔታ ያዳነው ተጠቃሽ ናቸው።

የእለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ኦሮሚያ ፖሊስን ከወልዲያ ከተማ አገናኝቶ ወልድያ ወደ አሸናፊነት የተመለሰበት የ2-1 ድል አስመዝግቧል። ወልዲያ በጨዋታው ቀዳሚ የሆነ ሲሆን በ28ኛው ደቂቃ ቢንያም ላንቃሞ ከመስመር የተሻማውን ኳስ በመጭረፍ አስቆጥሯል። ኦሮሚያ ፖሊስ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርግም ወልድያ ከተማ በፈጣን ቅብብል እና በረጃጅም ኳስ ወደ ግብ ሲደርሱ ተስተውሏል። በዚህም በ44ኛው ደቂቃ የወልድያው ከተማ ተጫዋች ቢኒያም ላንቃሞ ተከላካይ አታሎ አመቻችቶ የሰጠውን ኳስ ሊዮናርዶ ሰለሞን ወደ ግብ በመቀየር መሪነቱን ማስፋት ችሏል።

ከእረፍት መልስ ኦሮሚያ ፖሊስ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ይህንንም ተከትሎ በ78ኛው ደቂቃ ዳንኤል ዳርጌ ከፍፁም ቅጣት ክልል ውጪ አክርሮ በመምታት ማስቆጠር ችሏል። ጨዋታውም በወልዲያ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ምድብ ለ

የምድቡ የእለቱ የመጀመርያ ጨዋታ የምድቡ መሪ ነገሌ አርሲን ከአዲስ ከተማ ክ/ከተማ አገናኝቶ ነገሌ አርሲ ወደ አሸናፊነት የተመለሰበትን የ2-0 ድል አስመዝግቧል። ጀቤሳ ሚኤሳ እና ሙሉቀን ተስፋዬ የነጌሌ አርሲ ጎሎች ባለቤቶች ናቸው።

ደሴ ከተማ ከካፋ ቡና 2ለ2 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል። በሱፋቃድ ነጋሽ ሁለቱንም የደሴ ከተማ ጎሎች ሲያስቆጥሩ ያቤል ፍሬው እና ተረፈ ተሾመ ለካፋ ቡና አስቆጥረዋል።

ቦዲቲ ከተማ ከየካ ክፍለ ከተማ 1-1 ሲለያዩ ዘርዓይ ዘነበ ለቦዲቲ፣ ብስራት ታምሩ ለየካ ጎሎቹን አስቆጥረዋል። የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታም ደብረብርሀን ከተማ ከወሎ ኮምቦልቻ በተመሳሳይ 1-1 ሲጠናቀቅ ሄኖክ አየለ ለደብረብርሃን ፣ ሳሙኤል በለጠ ለኮምቦልቻ ጎሎችን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።

የሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ እና አጠቃላይ ውጤቶቹን ከታች ያለውን ሊንክ ተጭነው ያገኛሉ

Ethiopian Higher League 2023/24