ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | መቻል እና ንግድ ባንክ ድል አስመዝግበዋል

ዛሬ በተጀመረው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አምስተኛ ሣምንት ንግድ ባንክ እና መቻል ሲያሸንፉ ይርጋጨፌ እና ልደታ ነጥብ ተጋርተዋል።

ዛሬ ረፋድ ከአራት ሰዓት ጀምሮ በተደረጉ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ንግድ ባንክ እና መቻል የነገውን መርሃ ግብር እየጠበቁ ከደረጃ ሰንጠረዥ ከፍ ያሉበትን ድል አስመዝግበዋል።

ብዙም የግብ ሙከራዎች ባልታዩበት እና የመቀዛቀዝ ስሜት በነበረው በአራት ሰዓቱ ጨዋታ ይርጋጨፌ ቡና እና ልደታ ክፍለከተማ ነጥብ ተጋርተዋል።

የመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል የግብ ሙከራ ያልተደረገበት ሲሆን ልደታ ክፍለከተማ የኳስ ቁጥጥር ቢያደርግም ግብ ሳያስቆጥር 0ለ0 በሆነ ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል ገብተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ የጨዋታ ብልጫ በመውሰድ ኳስን ተቆጣጥረው የተጫወቱት ልደታዎች ከዕረፍት መልስ 5 ያህል ደቂቃዎች እንደተቆጠሩ በፊት መስመር ተጫዋቿ ህዳት ካሱ አማካኝነት ኳስን በመቀባበል ሄደው ባስቆጠሩት ግብ ቀዳሚ መሆን ችለዋል።

ግብ ከተቆጠረ በኋላ በሁለቱም ቡድኖች መካከል የመነቃቃት ስሜት ታይቷል። ልደታ ክፍለ ከተማዎች ተጫማሪ ግብ ፍለጋ ወደተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረስ ቢችሉም የይርጋጨፌ ተከላካዮች ኳስን በማስጣል በመልሶ ማጥቃት በመስመር በኩል እየገፋች በመሄድ በ65ኛው ደቂቃ እማቲ ደመላሽ ኳስና መረብ አገናኝታ አቻ ሆነው ነጥብ ተጋርተው እንዲወጡ አድርጋለች።

ከሰዓት ስምንት ሰዓት ላይ በተደረገው መርሐግብር በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩ ሦስት ግቦች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2ለ1 አሸንፏል።

ግቦች ገና በ4ኛው ደቂቃ መቆጠር በጀመሩበት በዚህ ጨዋታ የንግድ ባንክ የፊት መስመር ተጫዋች የሆነችው ሴናፍ ዋቁማ ኳስ እየገፋች በመሄድ ሳጥን ውስጥ ሆና ወደግብ የመታችውን ኳስ የኤሌክትሪኳ ተከላካይ ኳሱን ለመሸፈን ጥረት በምታደርግበት አጋጣሚ በእጇ ነክታ ፍፁም ቅጣት ምት በመሰጠቱ እመቤት አዲሱ ወደ ግብነት ቀይራው ንግድ ባንክ 1ለ0 መምራት ጀምረዋል።

በአስር ደቂቃዎች ውስጥም ተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን ሲያደርጉ የተሰተዋሉት ንግድ ባንኮች ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር የፈጀባቸው 4 ደቂቃ ብቻ ነበር። 8ኛው ደቂቃ ላይ መዲና አወል ኳስ እየገፋች የወሰደችውን ኳስ አክርራ በመምታት ታ ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችላለች።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአንፃሩ በመጀመሪያ አጋማሽ ጥሩ የማይባል እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን የንግድ ባንክ ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት ት በብልጠት በመጠቀም የምስራች ላቀው ግብ አስቆጥራ ዕረፍት 2ለ1 እየተመሩ እንዲወጡ አስችላለች።

በሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሙሉ የጨዋታ ብልጫ በመውሰድ ኳስን ተቆጣጥሮ በመጫወት የግብ ሙከራዎችን ሲያደረጉ የተስተዋሉ ሲሆን ንግድ ባንኮች የመከላከል ስልት በመጠቀም ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች ንግድ ባንክ 2ለ1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

በመጀመሪያው ቀን የመጨረሻ ጨዋታ መቻል በሰፊ የግብ ልዩነት ድሬዳዋ ከተማን አሸንፏል። ጨዋታው እንደተጀመረ ኳስን ተቆጣጠረው የጨዋታ ብልጫ የወሰዱት መቻሎች በ12ኛው ደቂቃ መሃል ሜዳ አካባቢ በተሠራ ጥፋት ቅጣት ምት አግኝተው ታሪኳ ዴቅሶ ቀጥታ ወደግብ መትታ በማስቆጠር መቻልን መሪ ማድረግ ችላለች።

ፍፁም የጨዋታ በላይነት የወሰዱት መቻሎች በመጀመሪያ አጋማሽ ብዙ የግብ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተስተውለዋል። የመጀመሪያ ግብ ካስቆጠሩ በኋላም ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር አራት ደቂቃ ብቻ ነበር የፈጀባቸው። በ17ኛው ደቂቃ ኪፊያ አብዱራህማን ከመስመር የተሻገረላትን ኳስ አየር ላይ እንዳለ በመምታት አስቆጥራው መቻሎች 2ለ0 እንዲመሩ አስችላ ነበር።

ዛሬ ጥሩ ያልነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች የመጀመሪያ አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃ ሲቀር እየተቀባበሉ በመሄድ በሊዲያ ጌትነት አማካኝነት ኳስና መረብ አገናኝተው 2ለ1 በሆነ ውጤት እየተመሩ ዕረፍት ወጥተዋል።

በመጀመሪያ አጋማሽ ያሳዩትን የጨዋታ የበላይነት በሁለተኛው አጋማሽም ያሳዩት መቻሎች ኳስን ተቆጣጠረው በመጫዎት ብዙ ግብ የሚሆኑ ኳሶችን አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። በ50ኛው ደቂቃ ተጨማሪ ግብ ፍለጋ በእርስ በርስ ቅብብሎሽ ወደ ተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል ጥሶ በመግባት በተከላካያቸው በአረጋሽ ፀጋ አማካኝነት ሶስተኛ ግብ አስቆጥረዋል።

እስከመጨረሻው ደቂቃ የጨዋታ በላይነት የወሰዱት መቻሎች የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ኳሶችን ወደፊት ገፍተው ሲጫወቱ ተስተውለዋል። በ60ኛው ደቂቃ ተቀይራ የገባችው ቤተልሔም ታምሩ እንደገባች በተሠራባት ጥፋት የተሰጠውን ቅጣት ምት በርቀት አክርራ ወደግብ በመምታት አስቆጥራው መቻሎች ተጨማሪ ግብ በማግኘት ተንበሽብሸው 4ለ1 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፈው እንዲወጡ አስችላለች።

የአምስተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ነገ ቀጥለው ሲደረጉ ረፋድ አራት ሰዓት በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ሜዳ ሀምበሪቾ ከአርባምንጭ ከተማ፣ ስምንት ሰዓት አዲስአበባ ከተማ ከ አዳማ ከተማ ፣ 10:00 ሀዋሳ ከተማ ከቦሌ ክፍለከተማ እንዲሁም በተመሳሳይ 10:00 በሀዋሳ ሰውሰራሽ ሜዳ ሲዳማ ቡና ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።