ፕሪምየር ሊግ | የ7ኛ ሳምንት ዐበይት ጉዳዮች

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሰባተኛው ሳምንት ጨዋታዎች ከትናንት በስቲያ ተገባደዋል ፤ በርካታ ትኩረት የሚስቡ ጉዳዮች ቢኖሩም ጥቂቶቹን እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል።

👉 ክስተቱ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሪነቱን አጥብቆ ይዟል

በኢትዮጵያ እግርኳስ አዲስ አዳጊ ክለቦች በዋናው ሉግ ሲቸገሩ ማየት የተለመደ ነው። በሊጉ  የሚገጥማቸው ፈተና ለማለፍ የታደሉ ክለቦችም ጥቂት ብቻ ናቸው። ባለፉት ዓመታት የጅማ አባ ጅፋር ፣ ፋሲል ከነማ እና መቐለ 70 እንደርታ ስም መጥቀስ ይቻላል። ባለፈው የውድድር ዓመትም ኢትዮጵያ መድን ለዋንጫ የሚፎካከር ቡድን ገንብተው አሳማኝ በሆነ መልኩ በሊጉ መቆየታቸው ይታወሳል። ዘንድሮም በሊጉ ክስተት የሆነ አንድ ክለብ አለ፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ!

ንግድ ባንክ አሁን ላይ በሊጉ ያልተሸነፈ ብቸኛው ክለብ ነው። ቡድኑ አምስት ጨዋታዎች ላይ አሸንፎ በተቀሩት ሁለት አቻ ተለያይቷል፤ በተለይም በተከታታይ ያስመዘገባቸው አራት ድሎች ቡድኑ ምን ያህል ኮስታራ የዋንጫ ተፎካካሪ እንደሆነ ማሳያ ነው። ንግድ ባንክ በሰባት ጨዋታዎች አስራ ሁለት ግቦች አስቆጥሯል፤  ይህ ቁጥርም አስራ አምስት ግቦች ካስቆጠሩት ፈረሰኞቹ እና አስራ ሦስት ግቦች ካስቆጠሩት የጣና ሞገዶቹ በመቀጠል ከፍተኛ የግብ መጠን ያስቆጠረ የሊጉ ክለብ ያደርገዋል። አራት ግቦች ብቻ ያስተናገደው የተከላካይ ክፍሉ ግን ጥቂት ግቦች በማስተናገድ የሊጉ ቀዳሚ ክለብ ያደርገዋል። የሊጉ ውድድር አንድ አራተኛ ላይ በደረስንበት በዚህ ወቅት ይህንን ጉዞ ማድረግ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጥሩ ስኬት ተደርጎ ይወሰዳል። ይህንን አካሄዱን አስቀጥሎ መዝለቅ እና ለብዙ ቡድኖች ዋና ችግር የሆነውን ጥሩ ውጤትን አስጠብቆ በወጥነት የመቀጠል ፈተና በምን አኳኋን ይወጣው ይሆን ? የሚለውን ጥያቄ በቀጣዮቹ የጨዋታ ሳምንታት የምንከታተል ይሆናል።

👉 የጦና ንቦቹ በአዲስ መልክ

በአዲሱ የውድድር ዓመት ክስተት ስለሆኑ ክለቦች ካነሳን በአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ስር ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኙትና የሚገባቸውን ያህል ትኩረት ስላልተሰጣቸው ወላይታ ድቻዎች ማንሳታችን ግድ ነው። በተለይም ጠንካራው ፋሲል ከነማን ባሸነፉበት ጨዋታ ያሳዩት እንቅስቃሴ የቡድኑ መሻሻል አንዱ ማሳያ ነው፤ የጦና ንቦች በጨዋታው የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ከመያዝ አልፈው ከተጋጣሚያቸው በተሻለ የጎል ሙከራዎችም አድርገዋል፤ በስድስተኛው ሳምንት ጨዋታ ሦስት ግቦች አስቆጥሮ ወደ ጨዋታው የቀረበውን የዐፄዎቹ የማጥቃት ክፍል ጥቃት የመከቱበት መንገድም የሚደነቅ ነበር። በጨዋታው ያሳዩት ብቃትም ከኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ቀጥሎ የውድድር ዓመቱ የቡድኑ ምርጡ እንቅስቃሴ ነበር ቢባል ማጋነን አይደለም።  የጦና ንቦቹ ባለፈው የውድድር ዓመት በተመሳሳይ ወቅት የሰበሰቡት ነጥብ አስራ አንድ ነበር፤ ዘንድሮም በተመሳሳይ አስራ አንድ ነጥቦች በመሰብሰብ  ደግመውታል። በውጤት ረገድ ተመሳሳይነት ቢኖረውም ቡድኑ እየተጫወተበት ያለው መንገድ ግን በጥሩነቱ ማንሳት ግድ ይላል። በተለይም ክለቡ ከዚህ ቀደም ከሚታወቅበት ቀጥተኛ አጨዋወት አውጥተው በወጣት ተጫዋቾች ማራኪ ቡድን የሰሩት አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹን አለማድነቅ አይቻልም። በተለይም ከ2013 ወዲህ ከዕድሜ እርከን ቡድኑ ብቅ ብሎ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች መሆን የቻለው አበባየሁ አጂሶ እንዲሁም በዕለቱ የቡድኑን ማሸነፊያ ጎል ያስቆጠሩት ዘላለም አባቴ እና ቢኒያም ፍቅሩ እያሳዩት ያሉት እድገት ብቻውን ወላይታ ድቻ ወጣቶችን ዕድል ከመስጠት ባለፈ እንደተጨዋች የሚታይ ዕድገት እያሳዩ እንዲቀጥሉ እና ወሳኝ ተጫዋቾች እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ ጥሩ እየተሳካለት እንዳለ ማሳያ ነው። ቡድኑ በወጥነት ውጤት ማምጣት ላይ ያለበትን ድክመት በሂደት ማስተካከል ከቻለ ደግሞ በወጣት ተጫዋቾች ወደ ውጤታማነት ማምራት እንደሚቻል ለሌሎች ምሳሌ የመሆን ዕድል አለው።

👉 ጦሩን የታደገው ሽመልስ በቀለ እና የታሪክ መገጣጠም

በኢትዮጵያ ታሪክ ከታዩ ምርጥ አማካዮች እንጥራ ከተባለ የሽመልስ በቀለን ስም መዝለል ከቶ አይቻልም። በእግር ኳስ ሕይወቱ ለዘጠኝ ክለቦች መጫወት የቻለው ይህ አማካይ ከዓመታት የሊቢያ፣  ሱዳንና ግብፅ ክለቦች ቆይታው በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ለመቻል ፊርማውን ማኖሩ ይታወሳል። ክለቡ አዳማ ከተማን ባሸነፈበት ጨዋታ አንድ ግብና አንድ ግብ የሆነ ኳስ በማቀበል ቡድኑ አሸንፎ እንዲወጣ የጎላ ድርሻ ተወጥቷል።
አሁን ልናነሳላቹህ የወደድነው ግን ስለ አንድ የታሪክ ግጥምጥሞሽ ነው፤ ተጫዋቹ ከዛሬ 13 ዓመታት በፊት ልክ በዚህ ሳምንት ማለትም ዲሰምበር ሁለት  ኢትዮጵያና ኬንያ በታንዛኒያ ብሔራዊ ስታዲየም  ባደረጉትና በኢትዮጵያ ሁለት ለአንድ አሸናፊነት በተጠናቀቀው የሴካፋ ዋንጫ ጨዋታ ላይ ተመሳሳይ ድንቅ የቅጣት ምት ግብ አስቆጥሮ ነበር። ከአስራ ሦስት ዓመታት በኋላም በተመሳሳይ ወቅት ሁለት ለአንድ በተጠናቀቀው ጨዋታ ኬንያ ላይ ካስቆጠራት ግብ ተመሳሳይነት ያላት የቅጣት ምት ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን ተሸክሞ ወጥቷል።

👉 በጎል ድርቅ የተመቱ የሊጉ ቡድኖች

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በጎል ድርቅ የተመቱ ቡድኖች ተበራክተዋል። ስድስት ቡስኖች ካደረጓቸው ሰባት ጨዋታዎች በሦስት እና ከዛ በላይ ጨዋታዎች ምንም ግብ ሳያስቆጥሩ ወጥተዋል። ሊጉ ከተጀመረ ገና ሰባተኛ ሳምንቱ ላይ ቢሆንም የቡድኖቹ ቁጥር መብዛት እና አብዛኞቹ የተመዘገቡ ቁጥሮች በተከታታይ መሆናቸው ግን ትኩረት ይስባል።

ሀድያ ሆሳዕና እና ሲዳማ ቡና በርከት ባሉ ጨዋታዎች ግብ ሳያስቆጥሩ በመውጣት ይመራሉ። ሆሳዕናዎች ካደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች በአምስቱ ኳስና መረብ አላገናኙም ፤ በሁለት ጨዋታዎችም ሦስት ግቦች ብቻ አስቆጥረዋል። ይህ ማለት በጨዋታ በአማካይ 0.4 ግቦች አስቆጥሯል ማለት ነው፤ ይህ ቁጥርም በሊጉ በጨዋታ ዝቅተኛ የግብ መጠን ያስቆጠረ ክለብ አድርጎታል።

በቅርቡ የአሰልጣኝ ለውጥ ያደረጉት ሲዳማ ቡናዎች ከሀድያ ሆሳዕና በተመሳሳይ በአምስት ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር አልቻሉም። ሲዳማዎች ወሳኝ አጥቂዎቻቸው በጉዳት ካጡ በኋላ ግብ ማስቆጠር አልቀናቸውም ፤ በተለይም የፍሊፕ አጃህ እና ይገዙ ቦጋለ ጉዳት የአጥቂ ክፍሉን አሳስቶታል፤ ከዛ በተጨማሪ የቡድኑ የፈጠራ አቅም መዳከም የራሱ ድርሻ አለው። ሲዳማዎች ከገጠሟቸው ሰባት ቡድኖች ሻሸመኔ ከተማ ላይ በሦስት ግቦች አቻ በተለያዩበት የወልቂጤ ከተማ ጨዋታ ደግሞ አንድ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በድምሩ በሰባት ጨዋታዎች አራት ግቦች አስቆጥረዋል። ይህ ማለት ቡድኑ በጨዋታ በአማካይ 0.5 ግብ በማስቆጠር ከሀድያ ሆሳዕና በመቀጠል ጥቂት ግብ ያስቆጠረ ቡድን ያደርገዋል።

ከሀድያና ሲዳማ ቡና በመቀጠል ሦስት ክለቦች ተቀምጠዋል። ሀምበሪቾ ፣ ኢትዮጵያ መድና እ ሻሸመኔ ከተማ በአራት ጨዋታዎች ላይ ኳስና መረብ ሳያገናኙ ወጥተዋል።  ሀምበሪቾዎች በመጨረሻዎቹ አራት ተከታታይ ሳምንታት ግብ አላስቆጠሩም፤ ቡድኑ በመጀመርያዎቹ ሦስት ጨዋታዎች አራት ግቦች አስቆጥሮ ሊጉን ቢጀምርም በሦስተኛው ሳምንት ዳግም በቀለ ካስቆጠራት ግብ በኋላ ኳስና መረብ ማገናኘት ተስኖታል።

ለሁለት ሳምንታት ግብ ሳያስቆጥሩ ቆይተው ያሬድ ዳዊት ባስቆጠራት ግብ አሃዱ ያሉት ሻሸመኔ ከተማዎችም በተመሳሳይ በአራት ጨዋታዎች ግብ ሳያስቆጥሩ ወጥተዋል። ቡድኑ ንግድ ባንክን በገጠመበት ጨዋታ ላይ ግብ አስቆጥሮ የ180 ደቂቃዎች የቆየው የጎል ረሃቡን ቢያስታግስም የአጥቂ ክፍሉ ጥራት ከፍ ማድረግ ይኖርበታል።

ወደ ሊጉ ባደጉበት ዓመት በርካታ ግቦች ማስቆጠር የቻሉት መድኖች ዘንድሮ ግን ኳስ እና መረብ የሚያዋህድላቸው ስል አጥቂ በማጣት ለተከታታይ አራት ሳምንታት ግብ አላስቆጠሩም። ቡድኑ ሀድያ ሆሳዕናን በገጠመበት ጨዋታ ላይ ከ360 ጎል አልባ ደቂቃዎች በኋላ በቹኩዌሜካ ጎድሰን ግብ አማካኝነት ወደ ግብ ማስቆጠሩ ተመልሷል። ሆኖም ባህር ዳር ከተማን ሦስት ግቦች አስቆጥሮ ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ማስቆጠሩ ሲታይ ግን የቡድኑ የማጥቃት ክፍል ምን ያህል እንደተዳከመ መገንዘብ ይቻላል። ሀዋሳ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማም በሦስት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ያላገናኙ ቡድኖች ናቸው።

👉 ከአምስት ሳምንታት ቆይታ በኋላ ከድል ጋር የታረቁት ብርቱካናማዎቹ የባለፈውን ውድድር ዓመት መጥፎው ክብረ ወሰን ከመድገም ተርፈዋል

በመጀመርያው ሳምንት ጨዋታ ሀምበሪቾን ሁለት ለአንድ ካሸነፉ በኋላ ለአምስት ሳምንታት ከድል ጋር ተኳርፈው የቆዩት የአሰልጣኝ አስራት አባተ ድሬዳዋ ከተማዎች ከ450 ደቂቃዎች ቆይታ በኋላ የመጀመርያ ድላቸው አሳክተዋል፤ ይህንን ተከትሎም የባለፈው ዓመት መጥፎ ክብረ-ወሰናቸው ከመጋራት ተርፈዋል። ባለፈው የውድድር ዓመት በተመሳሳይ ወቅት እስከ ሰባተኛው ሳምንት ድረስ አንድ ጨዋታ ብቻ ነበር ያሸነፉት፤ ኢትዮጵያ ቡናን ሦስት ለአንድ ያሸነፉበት ጨዋታም በሰባቱ ሳምንት ያስመዘገቡት ብቸኛ ድል ነበር። በዘንድሮ የውድድር ዓመት ግን ቁጥሩ ወደ ሁለት ከፍ በማድረግ መጥፎው ክብረ ወሰን ከመድገም ተርፈዋል።  ቡድኑ ባለፈው የውድድር ዓመት ተመሳሳይ ወቅት የሰበሰበው ነጥብ ስምንት ነበር፤ ዘንድም እስከ ሰባተኛው ሳምንት በዘለቀው መርሐግብር በተመሳሳይ ስምንት ነጥቦች እጁ ላይ አሉ። ባለፈው የውድድር ዓመት አምስት አቻ፣ አንድ ድል እና አንድ ሽንፈት አስመዝግቦ ነበር፤ ዘንድሮ ግን የድል ቁጥሩ ወደ ሁለት ከፍ በማድረግ በሦስት ጨዋታ ሽንፈት በተቀሩት ሁለት ደግሞ የአቻ ውጤት አስመዝግበዋል።
👉 የቅዱስ ጊዮርጊስ ቆራጥ ውሳኔ

ምንም እንኳን በቀጥታ ከ7ኛ ሳምንት ጋር ባይገናኝም ቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂው ሞሰስ ኦዶን የመቅጣቱ ዜና በሳምንቱ ዐበይት ጉዳይነት መነሳት ያለበት ነው። በ6ኛው ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ በባህር ዳር ከተማ በተረታበት ጨዋታ ገና በ 7ኛው ደቂቃ ለዱላ መጋበዙን ተከትሎ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣው ናይጄሪያዊ አጥቂ በአወዳዳሪው አካል የአራት ጨዋታ ቅጣት ተጥሎበት እንደነበር ይታወሳል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም ተጫዋቹ ባሳየው የሥነ ምግባር ግድፈት ምክንያት ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በተጫዋቾች የሥነ ምግባር መመሪያ መሰረት የቅጣት ውሳኔ ማስተላለፉን ይፋ አድርጓል።

ክለቡ በተጫዋቹ ላይ ያስተላለፈውን ቅጣት ዝርዝር ይፋ አለማድረጉ የሚደገፍ ባይሆንም ውሳኔን አለማድነቅ ግን አይቻልም። ተጫዋቾች በሜዳ ላይ በሚሰሩት ስህተት ቅጣቶች ሲጣሉባቸው በቡድናቸው ላይ የሚፈጥሩት ክፍተት የመኖሩ ነገር ግልፅ ቢሆንም በሀገራችን ክለቦች ለቅጣት ኮስታራ ሲሆኑ አይታይም። ይልቁኑም ከዳኝነት ስህተት እና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በማያያዝ የተበዳይነት ስሜታቸው ጎልቶ ሲታይ እና ችግሩን ወደ ሦስተኛ ወገን የማላከክ ከዚያም አለፍ ሲል ቅጣቶች እንዲነሱ ከተጨዋቾቻቸው ጎን በመቆም እስከ መወትወት ሲደርሱ ይታያሉ። ይህ አካሄድ የችግሩን ምንጭ ወደ ራሳቸው በመመልከት እንዳይፈልጉ ከመጋረዱ ባለፈ ተጫዋቾችም በሜዳ ላይ ስሜታቸውን ተቆጣጥረው ውሳኔዎቻቸውን እንዲያጤኑ ከማድረግ ይልቅ ኃላፊነት እንዳይሰማቸው የሚያበረታታ ነው። በመሆኑም ቅዱስ ጊዮርጊስ የወሰደው እርምጃ ክለቦች በተለይም በተጨዋቾች የሥነምግባር ችግር የሚመጡባቸውን ቅጣቶች በሰከነ ሁኔታ አጢነው አቋም መያዝ እንዳለባቸው ትምህርት የሚሰጥ ነው ማለት ይቻላል።