ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ | ነቀምቴ ሲሸነፍ አዲስ አበባ እና ቤንች ማጂ ቡና ድል አድርገዋል

የምድብ ‘ሀ’ ጨዋታዎች ዛሬ ሲከናወኑ አዲስ አበባ ከተማ ፣ ቤንች ማጂ ቡና እና ይርጋ ጨፌ ቡና ሦስት ነጥብ ማሳካት ችለዋል።

የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ በነቀምት ከተማ እና በቤንች ማጂ ቡና መካከል ተካሄዷል። በመጀመሪያው አጋማሽ ነቀምቴ ከተማ ግልፅ የሆነ ብልጫ በተጋጣሚው ቤንች ማጂ ቡና ላይ አሳይቷል። ጨዋታው እንደተጀመረ በ2ኛ ደቂቃ ነቀምቴዎች በጥሩ ቅብብል በመሄድ ግልፅ የግብ ዕድል ቢያገኙም ኢብሳ በፍቃዱ በግንባር ማስቆጠር ሳይችል አባክኖታል። በዚሁ አጨዋወት ነቀምቴ ተጨማሪ የግብ ዕድል ለመፍጠር ተጭነው ሲጫወቱ ተስተውሏል። በ12ኛው ደቂቃ ላይ ነቀምት ከተማ የፈጠረውን ሌላ የግብ ዕድል ሮኆቦት ስላሎ አስቆጥሯል። አጋማሹንም በዚሁ ውጤት በመጠናቀቅ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ቤንች ማጁ ቡና ከመጀመሪያው አጋማሽ እጅጉኑ ተሻሽሎ የተወሰደበትን የግብ ብልጫ ለመቀልበስ ሲጫወት ተስተውሏል። በአንፃሩ ነቀምቴ ከተማ በመጀመሪያ አጋማሽ ያስቆጠሩትን ግብ ለማስጠበቅ አፈግፍገው ተጫውተዋል። ሆኖም በ49ኛው ደቂቃ የቤንች ማጂ ቡናው ሀሰን ሁሴን ወደ ግብ የተመታን ኳስ ግብ ጠባቂው ሲመልስ መልሶ አሰቆጥሯል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ቤንች ማጂ ቡና ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ የበላይነት ወስዶ ተጫውቷል። በዚህም በ60ኛው ደቂቃ ቤንችማጂ ቡና ያገኘውን የግብ ዕድል ወንድማገኝ ኪራ ወደ ግብ መቀየር ችሏል። የጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ነቀምቴ ከተማ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ያደረገ ቢሆንም ሌላ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው በቤንች ማጂ አሸናፊነት ተጠናቋል።

የምድቡ ሁለተኛ ጨዋታ በይርጋ ጨፌ ቡና እና ጅማ አባ ጅፋር መካከል ተካሄዷል። በአጋማሹ ጅማ አባ ጅፋር በኳስ ቁጥጥሩ እና በማጥቃት ብልጫ ወስዶ ተጫውቷል። ይርጋጨፌ ቡና በመከላከል ረገድ ጠንካራ እና የተሻለ ሆኖ ተጫውቷል። በ41ኛ  ደቂቃ ጅማ አባ ጅፋሩ ተጫዋች ሄኖክ ገ/ህይወት ከመስመር የተሻገረውን ኳስ   በአስገራሚ ሁኔታ አስቆጥሯል። ጅማ አባ ጅፋር ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተጭኖ ሲጫወት ይርጋጨፌ ቡና በመልሶ ማጥቃት ለማስቆጠር ጥረት አርገዋል። የመጀመሪያ አጋማሽ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃ በ45+1 ደቂቃ ይርጋ ጨፌ ያገኘውን የመዕዘን ምት ጌታያውቃል ሮማን በግንባር አስቆጥሯል።

ከዕረፍት በኋላም ጅማ አባ ጅፋር ተመሳሳይ አጨዋወት አስመልክቶናል። በአንፃሩ ይርጋጨፌ ቡና በፈጣን መልሶ ማጥቃት ጥሩ ጥሩ የግብ ዕድል ሲፈጥሩ ተስተውሏል። ጨዋታው በዚሁ አጨዋወት ቀጥሎ በ89ኛው ደቂቃ ይርጋ ጨፌዎች ያገኙትን የግብ ዕድል ካሌብ ሽብሩ አስቆጥሮ ቡድኑ 2-1 እንዲያሸንፍ አድርጓል።

የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ በአዲስ አበባ ከተማ እና በስልጤ ወራቤ መካከል ተካሄዷል። በጨዋታው ፍጥነት እና ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ተመልክተናል። በ4ኛው ደቂቃ አዲስ አበባ ከተማ በፍጥነት ወደ ስልጤ ወራቤ የግብ ክልል ደርሶ የፈጠረውን የግብ እድል ቢንያም ፀጋዬ ከርቀት አስቆጥሯል። በቀጣይ ደቂቃዎችን አዲስ አበባ ከተማ በተደጋጋሚ ጫና በመፍጠር በ15ኛው ደቂቃ ቡይ ኮዌት በግል ብቃቱ ግሩም ግብ ማስቆጠር ችሏል። ስልጤ ወራቤ ተረጋግቶ ለመጫወት እና ውጤቱን ለመቀልበስ ጥረት ሲያረግ ተስተውሏል። ይህንንም ተከትሎ በ43ኛው ደቂቃ የስልጤ ወራቤ ተጫዋች የሆነው ብሩክ ሰማ የተሻገረለትን ኳስ ማስቆጠር ችሏል።

ከእረፍት መልስ የስልጤ ወራቤ የበላይነት የታየበት አጋማሽ ሆኖ ተመልክተናል። በአንፃሩ አዲስ አበባ ከተማ ያገኘውን የግብ ብልጫ ለማስጠበቅ ወደ ኋላ አፈግፍጎ ተጫውቷል ፤ ቡድኑ ተሳክቶለትም ውጤቱን አስጠብቆ መጨረስ ችሏል።

የምድቡ ጨዋታዎች ነገም በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ቀጥለው ሲደረጉ 03፡00 ላይ የምድቡ መሪ ነገሌ አርሲ ከ አዲስ ከተማ ክ/ከ ፣ 05፡00 ላይ ደሴ ከተማ ከ ካፋ ቡና ፣ 08፡00 ላይ ቦዲቲ ከተማ ከ የካ ክ/ከተማ እንዲሁም 10፡00 ላይ ደብረብርሃን ከተማ ከ ወሎ ኮምቦልቻ ይጫወታሉ።