ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ | ሸገር እና አርባምንጭ አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 6ኛ ሳምንት ዛሬ መደረግ ሲጀምር በምድብ ‘ለ’ ሦስት ጨዋታዎች ተደርገው አርባምንጭ ከተማ እና ሸገር ከተማ ድል አድርገዋል።

ረፋድ 4:00 ላይ አርባምንጭ ከተማን ከቢሾፍቱ ከተማ ያገናኘውን መርሐ ግብር አርባምንጭ 3ለ1 አሸንፏል።

ግቦች ገና ጨዋታው ከመጀመሩ መቆጠር በጀመሩበት በዚህ ጨዋታ አሸናፊ ተገኝ የምድቡ ፈጣን ግብ ማስቆጠር ችሏል። ጨዋታውን የጀመሩት ቢሾፍቱዎች የጨዋታ ቁጥጥር ለማድረግ ኳሱን ወደኋላ መልሰው ከግብ ጠባቂያቸው ጋር ለመጀመር ሙከራ በሚያደርጉበት ቅፅበት አሸናፊ ተገኝ ቀምቶ ኳስና መረብ በማገናኘት አርባምንጭ ከተማን መሪ አድርጓል።

ሆኖም ግን አርባምንጭ ከተማ በመጀመሪያ ግባቸው በመሪነት የቆዩት 2 ደቂቃ ብቻ ነበር። ግብ እንደተቆጠረባቸው የአቻነት ግብ ፍለጋ ጥቃት የጀመሩት ቢሾፍቱ ከተማዎች ኳስን ተቆጣጠሮ በጥሩ ቅብብሎሽ በ3ኛው ደቂቃ በፍሬገነት ኤርሚያስ አማካኝነት በተቆጠረ ግብ አቻ መሆን ችለዋል።

ከአቻነቱ ጎል በኋላም አርባምንጭ በድጋሚ መሪ ለመሆን ብዙ ደቂቃ አልፈጀበትም። በተደጋጋሚ ጥሩ ጥሩ ሙከራዎችን ሲያደርግ የታየው አህመድ ሁሴን በ11ኛው ደቂቃ ኳስና መረብን በማገናኘት አርባምንጭን ዳግም መሪ አድርጓል።

በሁለተኛ አጋማሽ ብዙ ለግብ የተቃረቡ ኳሶችን አግኝተው ሳይጠቀሙ የቀሩት አዞዎቹ የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ የጨዋታ ብልጫ መውሰድ ችለዋል። 70ኛው ደቂቃም ተቀይሮ የገባው 11ቁጥር ለባሹ ፍቃዱ መኮንን ከመስመር የተሻገረለት ኳስ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር 3ለ1 አሸንፈው እንዲወጡ አድርጓል።

ከሰዓት 8:00 ላይ በጀመረው መርሐ ግብር ሸገር ከተማዎች ባቱ ከተማን 2ለ0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የነገ መርሃ ግብር እስኪደረጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ላይ መቀመጥ ችለዋል።

የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ብልጫ በመውሰድ ኳስን ተቆጣጥረው የተጫወቱት ሸገር ከተማዎች ብዙ ለተከላካይ እና ለበረኛ ፈታኝ የሆኑ ኳሶችን ከርቀት ወደ ግብ ሙከራ ሲያደረጉ ተስተውለዋል። በ30ኛው ደቂቃ ላይ የሸገሩ የፊት መስመር ተጫዋች ሀይከን ደዋም ከመዋል ሜዳ አከባቢ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለውን ኳስ የባቱ ከተማ ተጫዋቾች ከጨዋታ ውጭ ነው በሚል ተዘናግተው ባሉበት ሁኔታ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር እረፍት 1ለ0 እየመሩ እንዲወጡ አስችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ቢሾፍቱ ከተማዎች የተጫዋቾች ቅያሪ አድርጎ ተሽሎ በመግባት የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም ግብ ማስቆጠር አልተቻላቸውም። ይልቁንም ሌላ የግብ እድሎችን ለመፍጠር የተቀንሳቀሱት ሸገሮች በአጥቂያቸው በፋሲል አስማማው አማካኝነት ከሳጥን ውጪ አክርሮ መጥቶ ባስቆጠራት ግብ 2 ለ0 በማሸነፍ የነገ መርሐ ግብሮችን እየጠበቀ የምድቡ አናት ላይ መቀመጥ ችለዋል።

የምድቡ የመጀመሪያ ቀን የመጨረሻ ጨዋታ በጋሞ ጨንቻ እና በኦሜድላ መካካል ሲደረግ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል። የመጀመሪያ አጋማሽ ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ የግብ ሙከራዎችን ሲያደረጉ የተስተዋሉት ጋሞ ጨንቻዎች በተደጋጋሚ የተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል ሲደርሱ ተስተውለዋል። ኦሜድላ በአንፃሩ በመልሶ ማጥቃት የግብ ሙከራዎችን ሲያደርጉ የተመለከትን ሲሆን ጥሩ ሆኖ የዋለው የተከላካይ ክፍላቸው በሁለቱም አጋማሽ ኳሶችን በቶሎ ከግብ ክልላቸው ሲያርቁ ተመልክተናል።

በ33ኛው ደቂቃ የጋሞ ጨንቻ የፊት መስመር ተጫዋች ያሬድ መኮንን ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ አክርሮ የመታት ኳስ ወደግብነት ተቀይራ እረፍት 1ለ0 በሆነ ውጤት እየመሩ ወተዋል።

 

በሁለተኛው አጋማሽ የአቻነት ግብ ፍለጋ ብዙ ሙከራው ሲያደረጉ የተሰተዋሉት ኦሜድላዎች በ52ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የሻማውን ኳስ ግዙፉ የተከላካይ መስመር ተጫዋቻቸው ዘካሪያስ በየነ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር አቻ እንዲሆኑ አስችሏል።

ውጤቱ አቻ ከሆነ በኋላ ጋሞ ጨንቻ ሌላ ግብ ፍለጋ ወደተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል ሲገቡ እና የግብ ሙከራዎችን የተመለከትን ሲሆን የኦሜድላን የተከላካይ መስመር አልፎ ሌላ ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።

የ6ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን አራት ጨዋታዎች ነገ ከረፋድ ጀምሮ ሀዋሳ አርተፊሻል ሜዳ የሚደረጉ ይሆናል። በዚህም መሰረት 03፡30 ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ንብ ፣  05፡30 ላይ ጅማ አባ ቡና ከ ኮልፌ ቀራኒዮ ፣ 07፡30 ላይ ሀላባ ከተማ ከ ሞጆ ከተማ እንዲሁም 09፡30 ላይ ኦሮሚያ ፖሊስ ከ ወልዲያ ይገናኛሉ።