የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ይቋረጣል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ከአምስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በኋላ እንደሚቋረጥ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

በዛሬው ዕለት በሀዋሳ ከተሳታፊ ክለቦች ጋር ውይይት ያደረገው ፌዴሬሽኑ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከሞሮኮ ጋር ለሚያደርገው የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ ዝግጅት ከቀጣዩ የአምስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በኋላ ሊጉ እንደሚቋረጥ አሳውቋል።

የአራት ሳምንታት ጨዋታዎች የተደረጉበት ሊጉ የአምስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ማክሰኞ እና ረቡዕ የሚደረጉ ሲሆን ፌዴሬሽኑ ውድድሩ መቼ እንደሚመለስ ባያሳውቅም የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች እስከሚደረጉበት ጥር ወር አጋማሽ ድረስ ተቋርጦ እንደሚቆይ ይገመታል።