የጣና ሞገዶቹ ተጫዋች ለወራት ከሜዳ ይርቃል

የባህር ዳር ከተማው የመስመር አጥቂ ባጋጠመው የACL ጉዳት ለወራቶች ከሜዳ እንደሚርቅ ታውቋል።

ባህር ዳር ከተማዎች ከ ሀዋሳ ከተማ ጋር ከሚያደርጉት የሊጉ ሰባተኛ ሳምንት ጨዋታ አስቀድሞ በሚያደርጉት የልምምድ መርሐግብር ወቅት የመስመር አጥቂው አደም አባስ ከበድ ያለ የጉልበት ጉዳት አጋጥሞታል።

አደም የህመሙን ሁኔታ ለመከታተል ወደ አዲስ አበባ በመምጣል ማርሻል ሆስፒታል እየተከታተለ ሲሆን እንደ ህክምና ባለሙያዎች ገለጻ ከሆነ የጋጠመውን የAnterior Cruciate Ligament (ACL) ጉዳት ለማከም ጉልበቱ ቀዶ ጥገና መደረግ እንዳለበት ተነግሮታል። አደም ቀዶ ጥገናውን አድርጎ ወደ መደበኛ ልምምድ ለመመለስ ከአራት ወራት በላይ እንደሚፈጅበት የተገለፀ ሲሆን በዚህም መሰረት የመስመር አጥቂው እስከያዝነው የውድድር ዓመት መጨረሻ ድረስ እንደታሰበው ወደ ልምምድ ከተመለሰ በመጨረሻ ጨዋታዎች ላይ ክለቡን ሊያገለግል እንደሚችል ተሰምቷል።