ፈረሰኞቹ ተጫዋቻቸው ላይ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፈዋል

ቅዱስ ጊዮርጊሶች ባሳለፍነው ሳምንት ባደረጉት ጨዋታ የዲሲፒሊን ጥሰት ፈፅሟል ባሉት ተጫዋች ላይ የቅጣት ውሳኔ ጥለውበታል።

በስድስተኛ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት መሸነፉ ይታወሳል። በዕለቱም በ7ኛው ደቂቃ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አጥቂ ሞሰስ ኦዶ ባሳየው ያልተገባ ባህሪ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ መውጣቱም ይታወቃል።

ክለቡ ዛሬ እንዳሳወቀው ከሆነ ሞሰስ ባሳየው የሥነ ምግባር ግድፈት ምክንያት በተጫዋቾች የሥነ ምግባር መመሪያ መሰረት የቅጣት ውሳኔ ማስተላለፉን አሳውቋል። ክለቡ የቅጣት ውሳኔ ማስተላለፉን ይግለፅ እንጂ ዝርዝር የቅጣት ውሳኔውን መጠን ከማብራራት ተቆጥቧል። ሶከር ኢትዮጵያ እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ ሞሰስ ክለቡን እና አጠቃላይ የቡድኑን አባላት ይቅርታ እንደጠየቀ የታወቀ ሲሆን ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት እንደተላለፈበት አውቀናል።

ናይጄሪያዊው አጥቂ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ መወደገዱን ተከትሎ አወዳዳሪው አካል የአራት ጨዋታዎች ቅጣት እንዳስተላለፈበት ይታወሳል።