ሪፖርት | ብርቱካናማዎቹ ከናፈቃቸው ድል ጋር ታርቀዋል

በሣምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር ድሬዳዋ ከተማ በቻርለስ ሙሴጌ ግቦች ሲዳማ ቡናን 2-0 በመርታት ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ተመልሷል።


የሣምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር ሲዳማ ቡናን ከድሬዳዋ ከተማ ሲያገናኝ ሲዳማዎች በስድስተኛው ሣምንት ከሀዲያ ጋር ያለ ግብ ከተለያየው ስብስብ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም አንተነህ ተስፋዬ እና ጸጋዬ አበራ አርፈው ጊት ጋትኩት እና ይገዙ ቦጋለ ገብተዋል። ድሬዳዋ ከተማዎች በአንጻሩ ከወላይታ ድቻ ጋር 1-1 ከተለያዩበት አሰላለፍ ዳዊት እስጢፋኖስን አስወጥተው በተመስገን ደረሰ ተክተዋል።

ምሽት 12 ሰዓት ላይ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታውን በተሻለ ግለት የጀመሩት ሲዳማዎች በመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች ሦስት ለግብ እጅግ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። ብርሃኑ በቀለ 5ኛው እና 9ኛው ደቂቃ ላይ ያደረጋቸው ሙከራዎች በግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ ሲመለሱ ከሁለተኛ ሙከራው ከሴኮንዶች በኋላ ደግሞ ደስታ ደሙ ከበዛብህ መለዮ በተሻገረለት ኳስ በግንባሩ በመግጨት ያደረገው ሙከራ በግቡ የላይ አግዳሚ ተመልሶበታል።

ሙሉ ብልጫ በመውሰድ በተደጋጋሚ የተጋጣሚን ሳጥን መፈተናቸውን የቀጠሉት ሲዳማ ቡናዎች 22ኛው ደቂቃ ላይም ጨዋታውን ለመምራት እጅግ ተቃርበው ነበር። ይገዙ ቦጋለ ከ ፍቅረኢየሱስ ተወልደብርሃን በተሰነጠቀለት ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር ቢገናኝም በጥሩ የጊዜ አጠባበቅ የወጣው ዳንኤል ተሾመ በግሩም ብቃት አግዶበታል። አጥቂው ከስድስት ደቂቃዎች በኋላም ከብርሃኑ በቀለ በተሻገረለት ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ከጨዋታ ውጪ ተብላ የተሻረች ግብ በግሩም ብቃት ማስቆጠር ችሎ ነበር።

30ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ደረሰን በጉዳት አጥተው በዘርዓይ ገብረሥላሴ የተኩት ድሬዳዋዎች በኳስ ቁጥጥሩም ይሁን የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ከፍተኛ ብልጫ ይወሰድባቸው እንጂ ለ10 ደቂቃዎች ያህል መነቃቃት ችለው ነበር። ሆኖም ግን የተጋጣሚያቸውን የግብ ክልል መፈተን አልቻሉም። የአጋማሹ መጠናቀቂያ ደቂቃ ላይም የሲዳማው የመስመር ተከላካይ ደስታ  ዮሐንስ እንደ ተመስገን ደረሰ ከንክኪ ውጪ ጉዳት አስተናግዶ ሊወጣ ተገዷል።

ከዕረፍት መልስ እጅግ ተሻሽለው በመቅረብ ብልጫ መውሰድ የቻሉት ብርቱካናማዎቹ 51ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ኤልያስ አህመድ በግሩም ዕይታ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ እየገፋ ሳጥን ውስጥ የደረሰው ቻርለስ ሙሴጌ በድንቅ አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

በቀሪ ደቂቃዎችም ጨዋታው በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ ብርቱ ፉክክር ቢደረግበትም ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ አልተደረገበትም ነበር። 60ኛው ደቂቃ ላይም የድሬዳዋ ግብ ጠባቂ የሆነው ዳንኤል ተሾመ በጉዳት በጨዋታው መቀጠል ባለመቻሉ ግብ ጠባቂው ሀምዲ ቶፊቅ በውድድር ዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሜዳ ገብቷል።

በሁለተኛው አጋማሽ እጅግ አስገራሚ በሆነ ብቃት በከፍተኛ ግለት በጨዋታው ብልጫ በመውሰድ መሪ ቢሆኑም አጥቅተው መጫወታቸውን የቀጠሉት ድሬዎች 81ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል። ዘርዓይ ገብረሥላሴ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ቻርለስ ሙሴጌ ኳሱ ዓየር ላይ እንዳለ በግሩም አጨራረስ ለራሱም ሆነ ለክለቡ ሁለተኛ ግብ አድርጎታል። ይህም የተሻለው የመጨረሻ ትዕይንት ሆኖ ጨዋታው በድሬዳዋ ከተማ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።


ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ አረጋይ ወንድሙ ተጭነው ለመጫወት አስበው እንደገቡ ይህም በተመሳሳይ ግለት አለመቀጠሉ ለመሸነፋቸው ምክንያት እንደሆነ ጠቁመው ለወደፊት ጥሩ ነገር እንዳለ ፍንጭ እንዳዩ እና ከጨዋታ ውጪ በመባል የተሻረው የይገዙ ቦጋለ ግብ ውጤት መቀየሩን በመናገር ግቡን የሻሩት የረዳት ዳኛው አቋቋም ልክ እንዳልነበር ገልጸዋል። የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ አሥራት አባተ በበኩላቸው ጠንካራ ጨዋታ እንደነበር ተናግረው በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ እንደተቸገሩ ከዕረፍት መልስ ግን ተሻሽለው እንደቀረቡ በመግለጽ ግብ አለማስተናገዳቸውን እንደ ጠንካራ ጎናቸው በመጠቆም የዛሬው ድል ለቀጣይ ጨዋታ መነሳሻ እንደሚሆናቸው ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።